የጫት አደገኝነትን ለማህበረሰቡ ለማስገንዘብ የሚረዳ ስልጠና ተሰጠ
“ራሳችን እና ሌሎችን ከጫትና ሌሎችም አደንዛዥ እፆች እየጠበቅን ብሩህ ተስፋ ያለው ትውልድ እንፍጠር፣ የአባቶቻችንን አደራ እንጠብቅ” በሚል መሪ ቃል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የፋርማሲ ትምህርት ቤት የፋርማኮሎጂ ት/ክፍል አማካኝነት የጫት መቃም መጠነ ሰፊ ጉዳትን በተመለከተ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በቆላድባ ከተማ ከየካቲት 18-20/2012 ዓ.ም ድረስ ስልጠና ተሰጠ፡፡

በስልጠናው በአካባቢው የሚገኙ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ወጣቶች እና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉ ሲሆን ጫት በማህበረሰቡ የሚያስከትለውን መጠነ ሰፊ የጤና ችግር፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ቀዉሶችን ነቅሶ በማውጣት ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ስልጠናው ከባህርዳር እስከ ጎንደር ድረስ ባሉ የተለያዩ ከተሞች በስፋት እየተመረተ የሚገኘውን የጫት ምርት እና ተጠቃሚነት በተለይም የነገ ሀገር ተረካቢ በሆነው ወጣት ትውልድ ላይ እያደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ ጉዳት ለማስገንዘብ ታስቦ ባለፈው ዓመት የተጀመረ እንደሆነና በዚህ ዓመትም ቆላድባ ከተማን ጨምሮ በሌሎችም አዳዲስ ከተሞች የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ስልጠናው በስፋት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፕሮጀክቱ አስተባባሪ እና የፋርማኮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ እሸቴ መለሰ ገልፀዋል፡፡

በስልጠናው ጫት በራሱ የሚያመጣው ተፅዕኖ እንዲሁም በኬሚካል ርጭት ምክንያት ከሚደርሰው ግለሰባዊ የጤና ችግር ባለፈ ማህበረሰባዊ እና ፖለቲካዊ ቀዉሱ ከፍተኛ መሆኑ እና በሀገራችን ጫትን በተመለከተ ግልፅ የሆነ የሚፈቅድም ሆነ የሚከለክል ህግ አለመኖሩ፣ በየአካባቢው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፋራዎች እና መዝናኛ ቦታዎች አለመበራከት እና ሌሎችም ለጫት መስፋፋት ተጠቃሽ እንደሆኑ ተገልጸዋል፡፡
ቀሲስ አሰፋ ሞላ የቆላድባ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፤ ስልጠናው በጣም መሰረታዊ እና ወቅታዊ እንደሆነ እና በጫት ምክንያት ወጣቱ እየደረሰበት ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ይረዳል ያሉ ሲሆን በኃይማኖት ተቋማትም የጫትን አስከፊነት በተመለከተ በስፋት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲም ይህንን ጉዳይ ጉዳዩ በማድረግ እየሰራ መሆኑ ሊመሰገን ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሌላው በስልጠናው ተሳታፊ የነበረው ወጣት ይሄነው ጆቫኒ፣ በስልጠናው በርካታ ዕውቀቶችን እንዳገኘ እና ለወጣቱ ለማስተላለፍ እንደሚሰራ የገለፀ ሲሆን ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ያለውን የጫት ሱሰኝነት ለማስቀረት ለመጭው ትውልድ አስፈላጊውን መልዕክት እናስተላልፋለን፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲም ይህንን መሰሉን ስልጠና አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ሲል ተናግሯል
በስልጠናው በሚገኙ ግብዓቶች መሰረትብ ተጎጁ በሆኑ የገጠር ቀበሌዎችና ሌሎችም አካባቢዎች የመስክ ስራ እንደሚሰራ እና አስፈላጊ መረጃዎችንም በመሰብሰብ እና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ለሚመለከተው አካል የማስተላለፍ ስራ እንደሚሰራ የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ገልፀዋል፡፡
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



