በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ስታትስቲክስ ትም/ክፍል “Proper Use of Statistical Software to Improve Research Skills” በሚል ርዕስ ለመሰናዶ መምህራን ስልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ስታትስቲክስ ትም/ክፍል አሀዛዊ መተግበሪያን/ Statistical Software / በአግባቡ በመጠቀም የምርምር ክህሎትን ለማሻሻል የሚያግዝ ስልጠና ከመጋቢት 04 – 6/2012 ዓ.ም በኮሌጁ የድህረ-ምረቃ አዳራሽ ተሰጠ፡፡

ስልጠናው በመሰረታዊ የኤስ.ፒ.ኤስ.ኤስ/SPSS / ጽንስ ሀሳቦችና አተገባበር በተለይም በመረጃ አዘገጃጀት፣ አጠቃቀምና አተናተን ላይ የሚያተኩር ሲሆን በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ስታትስቲክስ ትም/ክፍል መምህር በዶ/ር አራጋው እሸቴ፣ በዚሁ ትም/ክፍል ኃላፊና የስልጠናው አስተባባሪ በደሴ መለሰ እና በሌሎች የትም/ክፍሉ መምህራን ተሰጥቷል፡፡

የስልጠናው አስተባበሪ መ/ር ደሴ መለሰ እንደገለፁት ስልጠናው በሶስት ዙር የሚሰጥ ሲሆን በአሁኑ ዙር በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከተለያዩ ት/ቤቶች የተወጣጡ 30 የመሰናዶ መምህራን ተሳትፈዋል፡፡ ሁለተኛውና ሶስተኛው የስልጠና ዙርም በማዕከላዊና በምዕ/ጎንደር ዞን ለሚገኙ መምህራን በቀጣይ እንደሚሰጥ አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ የስልጠናውን አላማ አስመልክተው መ/ር ደሴ እንዳብራሩትም የመምህራን የተግባር ተኮር ምርምር አቅምን ለማጎልበት፣ መምህራን የስታትስቲክስ ሶፍትዌር በመጠቀም መረጃን በቀላሉ መተንተን እንዲችሉና ከመማር ማስተማር ጋር የተያያዙ ችግሮችን በሳይንሳዊ ጥናት በመፍታት የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ታስቦ የተሰጠ ነው፡፡

ስልጠናው አሀዛዊ መተግበሪያን በመጠቀም መረጃን በቀላልና በአጭር ጊዜ መተንተን እንደሚያስችላቸው አንዳንድ የስልጠናው ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡በፋሲለደስ ከፍተኛ ትም/መሰ/ት/ቤት መምህር ሀጎስ አስማረ እና በህዳር 11 ከ/ትም/መሰናዶ ት/ቤት መ/ር ያለው ሞገስ በተመሳሳይ ሀሳብ እንደተናገሩት ፣ ከዚህ በፊት ምርምር ሲሰሩ መረጃ የሚተነትኑት በማንዋል እንደነበር አስታውሰው በዚህ ስልጠና ምርምር ለመስራት መረጃዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ መተንተን የሚያስችል ሶፍት ዌር ላይ ጥሩ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡



