የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ ተከታታይ ውይይት እያካሄዱ ነው
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛና የሚመለከታቸው መካከለኛ አመራሮች በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ ከመጋቢት 7/2012 ዓ.ም ጀምሮ በሴኔት አዳራሽ ተከታታይ ውይይት እያካሄዱ ነው፡፡ በውይይቱ ተማሪዎችን ብሎም የግቢውንና የአካባቢውን ማህበረሰብ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመጠበቅ እያንዳንዱ ባለድርሻ ስለሚጠበቅበት ሃላፊነት፣ስለበሽታው መተላለፊያ፣ ምልክቶችና ቅድመ-መከላከያ ዘዴዎች በተመለከተ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ግብረ-ሀይሎችም ተቋቁመዋል፡፡

በወይይቱም መሰረት በተማሪ አገልግሎት ዲን በኩል ለምግብ ቤት ሰራተኞችና ለተማሪ መኝታ ቤት ተቆጣጣሪዎች የቅደመ-መከላለከያ ግንዛቤ የመፍጠር ሂደት በተከታተይ መሰጠት እንዳለበት እና እንዲሁም አመራሩ በኮሮና ቫይረስ መተላለፊያ ላይ አጽንዖት ሰጥቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆኑ ተገልጧል፡፡ በተሰጠው ሀገራዊ አቅጣጫ መሰረትም ለቀጣዮቹ 15 ቀናት የድጂታል ቤተ-መጽሀፍት አገልግሎትና የክፍል ውስጥ ትምህርት እንደማይሰጡ እና ስብሰባዎች በግቢው እንደማይካሄዱ አመራሩ አስታውቋል፡፡

በተለያዩ ግቢዎች ተንቀሳቅሰን እንዳየነውም በተለይ በዩኒቨርሲቲው ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና አጠ/ስፔ/ሆስፒታል ግቢ ላይ በሁሉም የተማሪ መመገቢያ አዳራሾች፣የመኝታ ክፍሎች፣ በቤተ-መጽሀፍትና በቢሮዎች በር ላይ አስፈላጊው የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ተሟልተው ተመልክተናል፡፡ የኮሌጁ አመራሮች አርአያ ሆነው እጃቸውን በመታጠብ ሁሉም የግቢው ማህበረሰብ ሲገባም ሆነ ሲወጣ እጁን በአግባቡ መታጠብ እንዳለበት አሳይተዋል፡፡

የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁና አጠ/ስፔ/ሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው ዩኒቨርሲቲው ከጤና ሚኒስቴር ጋር ወጭ በመጋራት አራት አዲስ አምቡላንሶችን እንደገዛ ጠቅሰው ከእነዚህም አንዱ አምቡላንስ በወቅቱ የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመከላከል ለሚደረገው ጥንቃቄ አገልግሎት እንደሚውል ገልጸዋል፡፡

ስራ አስኪያጁ አያይዘውም ከታካሚዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የሆስፒታሉ ሰራተኞች ተገቢ ጥንቃቄ አድርገው ህክምና እንዲሰጡ አስፈላጊው ማስክና የእጅ ንፅህና መጠበቂያ አልኮል መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



