የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት እና ምርምር ድጋፍ ለድርጅቶች
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን በሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ የማህበረሰብ አገልግሎት ፣ የምርምር እንዲሁም የቴክኖሎጅ ሽግግር ስራዎቹ ይታወቃል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከአማራ ብዙሀን መገናኛ ድርጅት በቀረበለት ጥያቄ መሰረት በአድማጮች ፍላጎት እንዲሁም በአማራ ኤፍ ኤም 105.1 ፕሮግራሞች ዙሪያ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ሀምሌ 25/2012 ዓ.ም በማራኪ ግቢ አልሙንየም ህንፃ የጥናት ውጤቱን እና የፕሮግራሞችን ይዘት፣ ቅርፅና ሳምንታዊ መርሀ ግብር በተመለከተ ከድርጅቱ ኃላፊዎች እና ሙያተኞች ጋር ምክክር አድርጓል፡፡

በምክክር መርኀ ግብሩ የጎንደር ኒቨርሲቲ ምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ፣ የምርምር እና ህትመት ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዘውዱ ተሸመ፣ የኮሌጅ ዲኖች እንዲሁም በጥናት እና ምርምሩ የተሳተፉ ምሁራን ተገንተዋል፡፡

መርሀ ግብሩን በንግግር የከፈቱት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ «የአማራ ብዙሀን መገናኛ ድርጅት ስራዎችን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ መስራቱ በጥናት ተመርኩዘን ተደራሽ ያልሁኑ ወረዳዎችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እና ለማህበረሰባችን ለውጥ በጋራ ለመስራት እንድንችል የረዳን ሲሆን ወደፊትም ከድርጅቱ ጋር በጋራ ለመስራት ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ፍላጎት አለው፡፡»ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአድማጮች ፍላጎት የዳሰሳ ጥናት ለአማራ ኤፍ ኤም 105.1 በሚል በማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ በጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር በአቶ አስማማው አዲስ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቧል፡፡

በፅሁፉ የአድማጮች የብዙሀን መገናኛ ፍላጎት፣ ፕሮግራሞችን ለመከታተል አመች የሆነውን ጊዜ፣ የአድሞጮች የፕሮግራም ይዘት ፍላጎት እና ለማድመጥ የሚፈልጉት የጊዜ ርዝማኔ እንዲሁም አቀራረብ ጥቆማ እና ምክረሀሳቦች ቀርበውበታል፡፡ በተጨማሪም በአቶ ምንይችል መሰረት የአማራ ኤፍ ኤም 105.1 ፕሮግራሞች ይዘት፣ ቅርፅ እና ሳምንታዊ መርሀግብር ቀርቦ ውይይት ከተካሄደ በኋላ መርሀግብሩ ተጠናቋል፡፡
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬትሐምሌ 25/2012 ዓ.ም



