ለካለን ብናካፍል የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ድጋፍ ተደረገ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለካለን ብናካፍል የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ነሀሴ 6/2012ዓ/ም 20 ኩንታል ጤፍ እና 17 ካርቶን ፓስታ ድጋፍ አደረገ፡፡

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በርካታ የማህበረሰብ አገልግሎቶች እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን፤ከነዚህም ውስጥ ለአረጋውያን እና ለአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማህበራት በተከታታይ የሚያደርጋቸው ድጋፎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ሸዋ ዳቦ አካባቢ የሚገኘው የካለን ብናካፍል የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል በ2010ዓ/ም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታማሚ የሌላቸውን ደካሞችን በማገልገል የተጀመረ ሲሆን፤ ሐምሌ 24/ 2010 ዓ/ም ህጋዊ ሰውነት አግኝቷል፡፡ ማህበሩ በሆስፒታል አስታማሚ የሌላቸውን ህመምተኞች በማስታመም፣ ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ ለአቅመ ደካሞች በተለያዬ መንገድ ድጋፍና አገልግሎት ሲሰጥ እንደቆየ የማዕከሉ መስራችና የበጎ ፈቃድ አገልጋይ የሆኑት ወጣት ዳዊት አየነው ገልጸዋል፡፤ ወጣት ዳዊት አያይዘውም በአሁኑ ሰዓት የከተማ አስተዳደሩ ማህበሩ እየሰጠው ያለውን ከፍተኛ አርአያነት ያለው አገልግሎት በመገንዘብ ቀበሌ 18 ሽዋ ዳቦ አካባቢ ለማዕከሉ ቦታ እንደሰጣቸው አውስተዋል፡፡

በዚህ ማዕከል 48 ለሚሆኑ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማንን፣ በራሳቸው መንቀሳቀስ፣ መመገብ፣ መጸዳዳት የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን አቅፎ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ወጣት ዳዊት አያይዘውም ወደፊትም ዩኒቨርሲቲው ይህን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደ አንድ የማህበረሰብ አገልግሎት ወስዶ ማዕከሉ በጅምር ላይ ያለ እንደመሆኑ ያለበትን ችግር ከጎናቸው ሆኖ እንዲደግፋቸው ጠይቀው፣ ስለተደረገላቸው ድጋፍ በማህበሩ ስም አመስግነዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲያችን የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ፣ የቴክኖሎጂ ኢኒስቲቲዩት ዲን አቶ ሰለሞን መስፍን፣ የማህበረሰብ አገልግሎት ይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፋንታው ከቦታው ድረስ በመገኘት ለማህበሩ የአመራር አካላት ድጋፉን አስረክበዋል፡፡

አንደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲም ያለውን ለማካፈል፣ በእውቀትም ሆነ በቁሳቁስ ለመደገፍ፣ ማዕከሉ የጀመረውን የገቢ ማመንጫም እገዛ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት የዩኒቨርሲቲያችን የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ በርክክቡ ላይ ተናግረዋል ፡፡



