የወተት ሀብት ልማትን ለማሳደግ የሚያስችል ስልጠና ለዘርፉ ሙያተኞች ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚንስቴር በመተባበር የወተት ላሞችን ምርታማነት ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኙ በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ይህ ፕሮጀክት ማለትም የአማራ ክልል የተቀናጀ የወተት ልማት ፕሮጀክት በሚሰራባቸው በምስራቅና ምዕራብ ደንቢያ ለሚገኙ የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች፣ የወተት ላም ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና ቆላድባ ከተማ ላይ ለሶስት ቀናት (ከነሀሴ 30- ጷጉሜ 2/2012 ዓ.ም) ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

የፕሮጀክቱን ዋና ዋና እንቅስቃሴዎች በማስተዋቀቅ ስልጠናውን የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው እንስሳት ህክምናና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ጸጋው ፈንቴ፣ ስልጠናውን በመስጠት በኩልም የነቃ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡

የእንስሳት ጤና ለወተት ምርታማነት ያለው ቀጥተኛ አስተዋጽኦ – የወተት ላም ጤናና አያያዝ፣ የወተት ላም ጤና ክትትልና ድጋፍ፣ የወተት ላም በሽታዎች መንስኤና መከላከያቸው እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ በስልጠናው ሳይንሳዊ ትንተና ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የክልሉን የወተት ሀብት ልማት ለማሻሻል በእንስሳት ጤናው ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን/ችግሮችን መለየትና ማሻሻል የሚቻልበትን መፍትሄ ማፈላለግ የስልጣናው ዋና አላማ መሆኑን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ሰፊነው አለሙና አቶ አዲሱ ጌጡ ገልጸውልናል፡፡ በቀጣይም መሰል ስልጠናዎች በሎሎች አካባቢዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስተባባሪዎቹ ተናግረዋል፡፡በመጨረሻም የመስክ ጉብኝት በማድረግ ስልጠናው ተጠናቋል፡፡



