በጎርጎራ ከተማ ልማት ኘሮጀክት ዙሪያ ዉይይት ተካሄደ
በቅርቡ በገበታ ለሃገር ለልማት በተመረጠቸው ጣና ዳር በምትገኘው ጎርጎራ ከተማ ላይ የጎንደር ዩኒቨርሲቲና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን መስከረም 23/2013 ዓ.ም የጋራ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በዚህ የጋራ ውይይት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጅነር አብርሃም በላይ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን፣ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ኃ/ማርያም፣ ሌሎች የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የጎንደር እና የባህር ዳር ዮ ዩኒቨርሲቲዎች ምክትል ፕሬዚዳንቶችና የተለያዩ ሙያዊ ዕውቀት ያላቸው ምሁራንና አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የጎንደር ዮኒቨርሲቲ ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳደር ጋር ያደረገው ውይይት ዓላማ በጎርጎራ ከተማና ጣና ዳር አካባቢ ላይ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተሰሩ ልዩ ልዩ የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን መነሻ በማድረግ በቀጣይ ጎርጎራን ጨምሮ በመተማ፣ አርማጭሆ፣ ወገራና በሌሎች የተመረጡ አካባቢዎች የመስክ ምልከታ በማድረግና የስራ እቅድ በማውጣት አካባቢውን በጋራ ለማልማት እንደሆነ ከውይይቱ መረዳት ተችሏል፡፡

ከውይይቱ በተጨማሪ ከጎርጎራ ከተማ መነሻውን ያደረገ ጉብኝት የተካሄደ ሲሆን፣ የጎርጎራ ተራራማ ቦታዎች፣ የሲሲኒዎስ ቤተ-መንግስት አካባቢና 6 ሺህ ሄክታር ቦታ እንዲያለማ ታስቦ የተገነባው የሰራባ የመስኖ ግድብ ዋና ዋና የጉብኝቱ አካል በማድረግ በስኬት ተካሂዷል ፡፡

ጎብኝዎችም በጉብኝታቸው መልካም እሴቶችና ስጋቶች ብለው ያሰቧቸውን በአስተያየት አንስተው በርዕሰ መስተዳድሩ በአቶ ተመስገን ጥሩነህ አማካኘነት ማደማደሚያ ተሰጥቶ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡



