ለፕሮጀክት ዋና አስተባባሪዎች የፋይናንስ አጠቃቀምን የተመለከተ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ2013 ዓ.ም ባወጣው የምርመር፣ የማህበርሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጅ ሽግግር ጥሪ ተወዳድረው ላሸነፉ የፕሮጀክቶች ዋና ተመራማሪዎች (PIs/ Principal Investigators) ስለ በጀት አጠቃቀምና ግዥ አፈጻጸም ስልጠና ተሰጠ፡፡
ስልጠናው የተጠሰጠው ህዳር 22፣ 2013 ዓ.ም በማራኪ ግቢ አልሙኒየም ህንጻ ሲሆን የየኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ ስልጠናውን በንግግር ከፍተዋል፡፡ በንግግራቸውም በዩኒንቨርሲቲው ተመራማሪዎች የሚቀርቡ የምርምር ንድፈ ሀሳቦች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸውን እንዲሁም በየአመቱ በመደበኛነት በመንግስት የሚመደበው በጅት እየጨመረ መሄዱን አውስተዋል፡፡ በመሆኑም የዩኒቨርሲቲው ምሁራን በምርምራቸው ለማምጣት ካሰቡት ዉጤት ላይ ለመድረስ፣ የሚያስፈልጓቸውን ግብአቶች ለማቅረብና አስፈላጊ የፋይናንስ ወጭዎችን ለመፈጸም የሚረዱ የፋይናንስና የግዥ መመሪያዎችን በሚገባ ማወቅና በአግባቡ ወደ ተግባር መቀየር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በተጨማም ከመደበኛ በጀት ወጣ ባለ መልኩ ከውጭ የሚገኙ የምርምር በጀቶች እየጨመሩ ነው፤ ስለሆነም ሁሉም መምህራን ለምርምር ስራ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባና ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚፈለግ እገዛ ካለም ም/ፕረዚዳንት ጽ/ቤቱና በስሩ ያሉ ዳይሬክቶሬቶች ዝግጁ መሆናቸውን ፕ/ር መርሻ ጠቁመዋል፡፡
የፋይናንስ መመሪያውን ማወቅ እና እንዴት መጠቀም እንደሚቻል፣ ለተለያዩ ስራዎች የሚያስፈልጉ ግብዐቶች በምን መልኩ መሟላት/መገዛት እንዳለባቸውና ከዚህ በፊት የነበሩ የኦዲት ግኝቶች እንዲሁም በኦዲት ግኝት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ዋና ዋና ክፍተቶች/መንስኤዎች በስልጠናው በስፋት ተዳሰዋል፡፡
የፕሮጀክት ሰነድ ከማወራረድ ጎን ለጎን የፕሪጀክቱን ውጤታማነት በተግባር ቀድሞ የማት አሰራር ቢኖር፣ ግብዐቶች እንደየ አስፈላጊነታቸው በፍጥነት እንዲሟሉ ማገዝ የሚችሉ አካላት ተባባሪ ቢሆኑ፣ የምርምር ፕሮጀክቶች ሰነድ በአንድ ጊዜ ከሚወራረዱ በየደረሱበት ደረጃ ከ2 – 3 ጊዜ የሚወራረዱበት መንገድ ቢመቻች፣ የምርምር እና ማ/ሰብ አገልግሎት ስራዎችን እንደ ሌላ ስራ ወይም ሁለተኛ ስራ የሚያዩ ባለሙያዎችና ሰራተኞች አልፎ አልፎ ስለሚታዩ እርምት ቢዎሰድ፣ በስራው ባህሪ ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት በቀላሉ በማይገኝባቸው ቦታዎች መኪና የሚመደብበት ወይም በኪራይ የሚሟላበት ሁኔታ ቢመቻች የሚሉትና እና የመሳሰሉት በውይይቱ ወቅት ከተነሱት ነጥቦች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ፋይናንስ አጠቃቀምን በተመለከተ የዩኒቨርሲቲው የፋናይናንስና በጀት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ሳህሌ፣ የግዥ አፈጻጸምን በተመለከተ የዩኒቨርሲቲው የግዥና ፋይናንስ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ በላይ ጥጋቡ እንዲሁም ኦዲትን በተመለከተ የዩኒቨርሰቲው የውስጥ ኦዲት ዳይሬክተር አቶ አምሳሉ አየነው ተመራማሪዎችን በማሰልጠን በኩል የነቃ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
ሰልጣኞች በበኩላቸው ስልጠናው በቀጥታ በሚመለካታቸው ሙያተኞች በመሰጠቱና ቀድሞ በመዘጋጀቱ ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ወደፊትም ለሌሎች ወጣት ተመራማሪዎች መሰል ስልጠናዎች ቢሰጥ ለምርምሩ ዘርፍ ውጤታማነት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
************************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙት ዳይሬክተር
ህዳር 24/2013 ዓ.ም







