በህግ ዙሪያ የስራ ላይ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁራን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጣቁሳ ወረዳ ለሚገኙ የቀበሌ ማህበራዊ ፍ/ቤት ዳኞችና አስተዳዳሪዎች የስራ ላይ አቅም ማጎልበቻ ስልጠና ከህዳር 25– 26/2013 ዓ.ም በደልጊ ከተማ ሰጥተዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ፋንታው፣ የዩኒቨርሲቶው የህግ ት/ት ቤት ተ/ዲን ዶ/ር ሰለሞን ተክሌ፣ የህግ ት/ት ቤት መምህርና የማህበረሰብ አልግሎት አስታባባሪ ዶ/ር ተፈራ እሸቱ፣ የጣቁሳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በለጠ ፈንቴ፣ የየቀበሌው አስተዳዳሪዎችና የማህበረሰብ ፍ/ቤት ዳኞች በስልጠናው ተሳትፈዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክትር አቶ ሰሎሞን የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም የዩኒቨርሲቲው የህግ ምሁራን የማህበረሰብ ፍ/ቤት ዳኞች በዘልማድ የሚሰሩበትን የህግ አግባብ በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ለማስቻል በደልጊ ተገኝተዋል፡፡ የማ/ፍ/ ቤት ዳኞች ለአካባቢያቸው ማህበረሰብ ከስልጣናው በሚያገኟቸው እውቀቶች ተመስርተው በሚመለከታቸው ጉዳዮች ፍትሀዊ ዳኝነት እንዲሰጡ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡
የማህበረሰብ ፍ/ቤት ዳኞች በየቀበሌው ተቋቁመዋል፤ የማህበራዊ ፍ/ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ 246/2009 እና በፊት የነበረው አዋጅ 151/2000 እንደሚለው “ማንበብና መጻፍ” የሚችል ማንኛውም ግለሰብ የዚህ የማህበራዊ ፍ/ቤት ዳኛ መሆን ይችላል ይላል፡፡ ነገር ግን “የህግ እውቀት” ያለው ሰው አይልም፤ በመሆኑም ይህንን ክፍተት ለመሙላት ይህ ስልጠና አንዳስፈለገ ዶ/ር ሰሎሞን ገልጸዋል፡፡
ስልጠናውን በመስጠት በኩልም አንጋፋዎቹ የህግ መምህራን ዶ/ር ሰሎሞንና ዶ/ር ተፈራ የነቃ ተሳትፎ አድገዋል፡፡ መሰል ስልጠናዎች በሌሎች አካባቢ ለሚገኙ የማህበረሰብ ፍርድ ቤት ዳኞች እንደሚሰጥ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ያነጋገርናው ሰልጣኞች፣ ስልጠናው የነበረባቸውን የህግ ክፍተት በመሙላትም ሆነ ያላቸውን የህግ ኃላፊነትና ተጠያቂናት በግልጽ እንዲመለከቱ አንደረዳቸው ገልጸዋል፡፡
******************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ህዳር 26/2013 ዓ.ም







