የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አቀፍ አማካሪ ምክር ቤት የመጀመሪያው ጉባኤ ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት በከፍተኛ ተቋማት ሰላማዊ የሆነ የመማር ማስተማር ተግባር እንዲኖር እና ተማሪዎች የመጡበትን ዓላማ አሳክተውና ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ የመጡበት እንዲመለሱ የሚያስችል የአማካሪ ምክር ቤት አቋቁሟል፡፡
ይህ አማካሪ ምክር ቤት ታህሳስ 1/2013ዓ.ም በማራኪ ግቢ አልሙኒም አዳራሽ የመጀመሪያውን ውይይት አካሂዷል፡፡ አማካሪ ምክር ቤቱ በተደራጀና መደበኛ በሆነ መንገድ መቋቋሙ የ2013ዓ.ም የትምህርት ዘመን ዘላቂ የሆነ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን የተቋሙን ተልዕኮ ለማሳካት የሚያግዝ አይነተኛ መንገድ መሆኑ በተሳታፊዎች ተጠቁሟል፡፡
በውይይቱ አቶ ሞላ መልካሙ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የአማካሪ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ፣ አቶ አወቀ አስፈሪ የጎንደር ከተማ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊና የአማካሪ ምክር ቤቱ ም/ሰብሳቢ፣ ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ም/ኘሬዚዳንትና የፕሬዚዳንቱ ተወካይ እንዲሁም የአማካሪ ምክርቤቱ ፀሀፊ፣ አቶ ባዩ በዛብህ የጎንደር ከተማ የሰላምና ልማት ሸንጎ ሰብሳቢ እና የሸንጎው አባላት፣ ኮማንደር አየልኝ ታክሎ የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ፣ የጎንደር ከተማ የሃይማኖት አባቶች፣ ከጎንደር ከተማ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ወጣቶችና ከብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እና ሌሎችም አባላት ተገኝተዋል፡፡
ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ የአስተዳደር ም/ፕሬዚዳንት የሆኑት ፕሮፌሰር ጋሻው አንዳርጌ ስለአማካሪ ምክር ቤቱ አደረጃጀት፣ ተግባርና ኃላፊነት በተመለከተ እንዲሁም በ2012ዓ.ም በዩኒቨርሰቲው የተከሰቱ ችግሮችን፣ መንስኤና ያስከተለውን ጉዳት፣ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ተመራቂ ተማሪዎችን እና ሌሎች ተማሪዎችን ለመቀበል ያደረገውን ቅድመ ዝግጅት በሚመለከት ለተሳታፈዎች በፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ በቀረበው የመወያያ መነሻ ፅሁፍ ላይም ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
የ2013 የትምህርት ዘመን በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም የአማካሪ ምክር ቤት አባላት የበኩሉን ሀገራዊ ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸውና ካለፈው በጀት አመት ትምህርት በመውሰድ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ምልክቶችን በጥንቃቄ በማጤንና የችግሮችን ምንጭ በመለየት ባሉበት እንዲከስሙ የማድረግ ስራ መስራት አለበት በማለት ተቀዳሚ ከንቲባው በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአለፈው ዓመት የተጀመረውን አንድ ተማሪ ለአንድ ወላጅ የሚለውን የቤተሰብ ፕሮጀክትን መልካም ተሞክሮ በዚህ ዓመትም ተጠናክሮ መቀጠል እንደለበት በመግለፅ ውይይቱንን አጠናቀዋል፡፡
********************************************************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ታህሳስ 02/2013 ዓ.ም







