የሁለተኛው ዙር የመስክ የቡድን ስልጠና/TTP / ‘ኦረንቴሽን’ ተሰጠ
በዚህ አመት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት ለሚሰሩት የመስክ የቡድን የተግባር ስልጠና ፕሮግራም ታህሳስ 5/2013 ዓ.ም በኮሌጁ አዳራሽ የቅድመ ተግባር ስልጠና/ኦረንቴሽን/ ተሰጠ፡፡ በመድረኩ ተማሪዎችን በተግባር ስልጠና ቆይታቸው ሊያግዙ የሚችሉ በርካታ ገለጻዎች በተለያዩ ምሁራን የተሰጡ ሲሆን በዋናነትም የመስክ የቡድን ስልጠና ታሪካዊ አመጣጥ፣ፋይዳና ተግባራት፣ የአካባቢና ማህበረሰብ ጤና ፣የኮቪድ -19 ቅድመ ጥንቃቄ እንዲሁም የአነስተኛ ፕሮጀክት ጽንሰ ሀሳብ የሚሉት ጉዳዮች ላይ ለተማሪዎች ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ በገለጻዎቹ ላይም ውይይት ተደርጓል፣ከተማሪዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከተመሰረተ ጀምሮ እንደ አንድ የጤና ፍልስፍና አድርጎ ተግባራዊ ሲያደርገው ለአመታት የዘለቀው የመስክ የቡድን ስልጠና /Team Training Program / መኖሩ ይታወቃል፡፡ይህም የህክምናና የጤና ሳይንስ ተማሪዎች ከመመረቃቸው አስቀድመው በህብረተሰቡ ውስጥ በመግባት የጤናና ተያያዥ ችግሮችን የመለየት፣የማስተባበርና በችግሮቹ ላይ ያተኮሩ አነስተኛ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ መፍትሄ መስጠትን የሚለማመዱበት ፕሮግራም ነው፡፡
********************************************************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ታህሳስ 5/2013 ዓ.ም







