የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ማኔጅመንት የትምህርት ክፍል በአራት የተለያዩ ሀገር በቀል የቱሪዝም መስኮች ስልጠና መስጠት ጀመረ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ማኔጅመንት የትምህርት ክፍል ሀገር በቀል እውቀቶችን በመጠቀም አዳዲስ የቱሪዝም መስኮችን የማጎልበትና የመፍጠር ንድፈ ሃሳብን በተመለከተ፣ ሀገር በቀል የስዕል አሳሳል ጥበብን፣ የብራና አዘገጃጀትና አጠቃቀምን እንዲሁም የሸክላ ሥራ ሙያዎችን በተመለከተ ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፈንታው እንደገለጹት ሀገራችን በርካታ የቱሪዝም መስህብ ሃብትና የቱሪዝም መዳረሻ ያላት ብትሆንም ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው በቂ የሆነ ጥቅም አግኝታለች ብሎ ለመናገር አይቻልም ብለዋል፡፡
የሀገር ጎብኝዎች ወደ ሌሎች ሀገራት የሚጓዙበት ዋና ምክንያት የሌሎችን ባህል፣ታሪክና የሀገር በቀል ዕውቀት ውጤቶችን ለማወቅና ለመግዛትም ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ የቱሪዝም መስክ የተሰማሩ ግለሰቦችም ሆኑ ባለሙያዎች የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ ማራዘም የሚያስችሉ ሀገር በቀል እውቀቶችን በመጠቀምና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ምቹ በማድረግ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ጥቅም ለማግኘት መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ አብራርተዋል፡፡ አቶ ሰለሞን በመጨረሻም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሀገራችን ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን በማሰብ በጥናት ላይ የተመሰረተ አጫጭር ስልጠናዎችን በማዘጋጀት ያቀረበ ሲሆን ሰልጣኞችም ከዚህ ሙያዊ ስልጠና በቂ አውቀት ታገኙበታልችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት የፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ እንግዱ ገብረወልድ በበኩላቸው ከስልጠናዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ለዞንና ለከተማ የባህል ቱሪዝም ባለሙያዎች የሚሰጠው ነባር የቱሪዝም መስኮችን የማበልፀግና አዳዲስ መስህቦችን የማስፋፋት ንድፈ ሀሳብ ስልጠናው ለሁለት ቀናት የሚሰጥ ሲሆን ሌሎች የብራና፣ የሸክላ ስራና የሀገር በቀል ስዕል አሳሳል ሙያዎች ስልጠና ለአምስት ቀናት ያህል እንደሚሰጡ አስረድተዋል፡፡

ስልጠናው ከግንቦት 03 እስከ ግንቦት 07/2013 ዓ.ም. በፋሲል የመዋኛ ግቢ ዞብል የስነ-ጥበብ ማዕከል ውስጥ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡




