በባህላዊ ህክምናና በአእምሯዊ ንብረት አጠባበቅ ዙሪያ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ተካሄደ
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያና ከአለም አእምራዊ ንብረት ድርጅቶች ጋር በመተባበር በባህላዊ ህክምናና በአእምሯዊ ንብረት አጠባበቅ ዙሪያ ግንቦት 2 እና 3/2013 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡
በምክከር መድረኩ ከደቡብ አፍሪካና ከጀኔቫ ሀገራት የተለያዩ ምሁራን በበይነ መረብ ተሳትፈዋል፤ በተጨማሪም ጥሪ የተደረገላቸው የባህል ህክምና አዋቂዎችና የክልሉ ጤና ቢሮ አመራሮች፣ከጎንደርና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ምሁራንና የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ በዚህ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ የባህል ህክምናና አእምሯዊ ንብረት አጠባበቅ ላይ ትኩረት ያደረጉ የምርምር ሀሳቦችና ጽሁፎች በተለያዩ የውጭና የሀገር ውስጥ ምሁራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፤የባህል ህክምና አዋቂዎችም ባህላዊ የመድሀኒት ቅመማ ሂደታቸውን በመድረኩ አብራርተዋል፡፡

ባህላዊ ህክምናዎች በዘመናዊ ህክምና ማእከላት እንደሚሰጡ የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮወች መኖሩን የገለጹት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ም/ ኃላፊ ዶ/ር ህይወት ደበበ እነዚህ ሀገርበቀል ህክመናዎች በህብረተሰቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የደቡብ አፍሪካን ተሞክሮ አንስተዋል፡፡ በሀገራችንም ለባህል ህክምና ያለው እይታ እንደሀገር በጎ ቢሆንም የባህል ህክምናውንና አዋቂዎቹን ከመደገፍና ከማዘመን አንጻር ውስንነት መኖሩን ዶ/ር ህይወት ገልጸው የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ ማየት ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የባህል ህክምናዎችን ለማዘመን ጥሩ መንገድ እንደሚከፍት ተናግረዋል፡፡
የዘመናዊ ህክምና መሰረቱ ባህላዊ ህክምና እንደሆነ ያብራሩት የፋርማሲ ት/ቤት ኃላፊና መምህር አቶ አብዮት እንዳለ አብዛኛው የማህበረሰባችን ክፍል መሰረታዊ ጤናውን የሚጠብቀው በባህላዊ ህክምና መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጅ ለባህል ህክምናና እና ለአዋቂወቹ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ ነው፡፡ ስለሆነም የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ ለመጋራት፣ ደህንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠና ዘመኑን የዋጀ የባህል መድሀኒት በብዛት ለገብያ ለማቅረብ፣ እንዲሁም የባህል ህክምና አዋቂዎችን የአእምሮ ንብረት ለማስጠበቅ የውይይት መድረኩ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አቶ አብዮት አክለው ተናግረዋል፡፡

“የባህል ህክምና በሚስጥር የሚያዘው በቀደሙት ነገስታት ይነቀፍ ስለነበር ነው፣” ያሉት የአማራ ክልል የባህል መድሀኒት ህክምና አዋቂዎች ማህበር ፕሬዚዳንትና የባህል ህክምና ባለሙያ ሊቀ ጠበብት ምወደው አዘዘው፣ከዚህ ሌላ ግን “የባህል መድሀኒት ብዙ ሰው ሲያውቀው ይረክሳል” የሚለው ሀሳብ ኋላ ቀር አመለካከት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “የሚያድን መድሀኒት ምንጊዜም ያድናል፣” ያሉት ፕሬዚዳንቱ ብዙ መድሀኒት ማወቅና ከማግበስበስ ይልቅ በአንድ መድሀኒት ላይ ጥልቅ ግንዛቤና የባለቤትንት መብት በመያዝ ከአምራች ፋብሪካዎች ጋር ስምምነት በመፈጸም በቂ የኢኮኖሚ ምንጭ ማግኘት እንደሚቻልም አብራርተዋል፡፡



