የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርትን ከምርምር ጋር በአንጋፋ ተመራማሪዎች ማቀፍ ወይም ማሰራት (Linking Phd Programs with Research through Senior Investigator and Research Group Approch) በሚል ርእስ አውደ ጥናት ተካሄደ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፅ /ቤት የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርትን ከምርምር ጋር በአንጋፋ ተመራማሪዎች ማቀፍ ወይም ማሰራት (Linking Phd Programs with Research through Senior Investigator and Research Group Approch) በሚል ርእስ ግንቦት 16/2013ዓ/ም በሴኔት አዳራሽ አውደ ጥናት አካሂዷል፡፡

በዕለቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ፣ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ፣ የምርምርና ህትመት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ምሳዬ ሙላቴ፣ ዲኖች፣ የድህረ ምረቃ አስተባባሪዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡
የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ በወርክሾፑ የመክፈቻ ንግግራቸው በድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችና በምርምር በጀት ምደባ ላይ ክፍተቶች በመኖራቸው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት ከአካዳሚክ ቢሮው ጋር በመቀናጀት የምርምሩንና የድህረ ምረቃ ትምህርቱን በአንድ ላይ በማስተሳሰር ጥሩ ምርምር ተሰርቶ ጥሩ መማር ማስተማር ማካሄድ እንዲቻል በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በመቀጠል በዩኒቨርሲቲው የድህረ ምረቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በዶ/ር አስማማው አለሙ current status/ challenges of postgraduate funding፣ የውጭ ግራንት ማኔጅመንት ኦፊሰር በሆኑት በዶ/ር ነፃነት ወርቁ The concept of post-doc በሚል ገለፃ የቀረበ ሲሆን፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት በዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ ደግሞ Linking Phd Programs With Research through Senior Investigator and Research Group Approch በሚል ገለፃ ቀርቧል፡፡ የቀረቡትን ፅሁፎች መነሻ በማድረግ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ወደፊት በአንጋፋ ተመራማሪዎች የሚመራና የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን እንዲሁም ፖስት ዶክተራል ተማሪዎችን ያካተተ የምርምር ቡድኖች በየኮሌጁ ተቋቁመው፣ የምርምር በጀት ተመድቦላቸው ሰፊ፣ችግር ፈቺና ጥራት ያለው ምርምር መስራት እንዲችሉ ሰፊ ስራ እንደሚሰራ ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ ገልፀዋል፡፡
ለፒ ኤች ዲ ምርምር የሚመደበው በጀት አነስተኛ በመሆኑ ተማሪዎች ጥራት ያለው ምርምር ለማካሄድ ሲቸገሩ እንደሚታዩና ይህንን ችግር ለመቅረፍና ጥራቱን ለማሻሻል ከአንጋፋ ተመራማሪዎች ስር ሆነው የምርምር በጀት ተመድቦላቸው እንዲሰሩ ለማድረግ አላማ ያደረገ አውደ ጥናት መሆኑን የምርምርና ህትመት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ምሳዬ ሙላቴ ገልፀዋል፡



