“Implementation Research on CRC” በሚል ርዕስ አውደ ጥናት ተካሄደ
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከጤና ሚኒስቴርና ከአለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር “Implementation Research on CRC” በሚል ርዕስ “ሲ አር ሲ”/compassionate and respectful care / ላይ ስለሚሰሩ ጥናቶች የመረጃ ትንተና እና ትግበራ የሚመለከት አውደ ጥናት ከግንቦት16-20/2013 ዓ.ም አካሄደ፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር በጤና ስርዓቱ ውስጥ ሩህሩህ፣ተንከባካቢና አገልጋይ/ compassionate and respectful care / የጤና ባለሙያዎችን ለመፍጠር እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም በፕሮግራም ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለይቶ ለቀጣይ ትግበራው አዳዲስ አሰራሮችን ለመዘርጋት እየተሰራ በሚገኘው ፕሮጀክት የምርምር ውጤቶች አጻጻፍ የተመለከተ አውደ ጥናት በዚህ ሳምንት አካሂዷል፡፡

በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ የተገኙት የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ “በዩኒቨርሲቲው የሚሰሩ ምርምሮች ለማህበረሰቡ እና ለፖሊሲ አውጭዎች ትርጉም ያለው ጠቀሜታ እንዲሰጡ አተኩረን እንሰራለን” ብለዋል፡፡ ስለሆነም አንድ ተመራማሪና የችግሩ ባለቤት ከሆኑ ሴክተር መስሪያ ቤቶች አንድ ሰራተኛ በጋራ በመሆን ለችግሮች መፍትሄ እንዲያመጡ እየተሰራ መሆኑንም ዶ/ር ቢኒያም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ስር ስድስት ንዑስ ፕሮጀክቶች ያሉ ሲሆን በእያንዳንዱ ንኡስ ፕሮጀክት ከተመራማሪ፣ከጤና ጥበቃ ከፒ ኤች ዲ ተማሪ ስብጥር ያከተተ እንደሆነ ያብራሩት የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ቢኒያም፣ የዚህ አሰራር ዋና አላማም ከዚህ በፊት የሚሰሩ የምርምር ውጤቶችን ለመተግበር ብዙ ችግሮች እያጋጠሙ ስለሆነ ተግባሪዎችን በምርምር ሂደቱ በማሳተፍ መፍትሄ አፈላላጊ እንዲሆኑ በኋላም እንዲተገብሩ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የፕሮግራሙ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አብዩ ጌታ በበኩላቸው ሩህሩህና አክብሮት የተላበሰ የጤና ባለሙያዎች አገልግልት የትግበራ ጥናት ላይ የተካሄደው ስልጠና በስድስት የጥናት አርዕስት ላይ የተሰበሰበውን መረጃ በአግባቡ ለመጻፍና ለመተንተን ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል፤ ስለሆነም “የጥናቱ ግኝት በጤና ስርአቱ ሩህሩህና አክብሮት የተሞላበት የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ይረዳል” ሲሉም አክለዋል፡፡
“ህይወትን በማዳን በኩል ስለሚወሰዱ የመፍትሄ ተግባራት ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ነው፤ ስለሆነም የምርምር ውጤቶች የትግበራ ሳይንስ መኖር የጥናት ፈጻሚዎችና ፖሊሲ አውጭዎች የጤና ስርዓቱን እክሎች በመለየት በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ እንዲሰጡ ያግዛል፣” ሲሉ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፕሮግራሙ አስተባባሪ ዶ/ር አለማየሁ ተክሉ አብራርተዋል፡፡
ከአምስት ቀናት የአውደ-ጥናት ቆይታ በኋላ ሁሉም የምርምር ቡድኖች የምርምር ውጤታቸውን አቅርበው በግምገማው ሂደት የተመረጡ አስር ምርምሮች በአለም አቀፍ ጆርናል ላይ ልዩ ትኩረት የሚሹ ሆነው እንደሚወጡም ተጠቁሟል፡፡



