በመሰረታዊ ሂሳብ መዝገብ አያያዝና ፋይናንስ አስተዳደር ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል በመሰረታዊ ሂሳብ መዝገብ አያያዝና ፋይናንስ አስተዳደር በሚል ርዕስ ለደባርቅ ወረዳና ለአማራ ብደርና ቁጠባ ተቋም (አ.ብ.ቁ.ተ) ደንበኞች ግንቦት 19 እና 20/2013ዓ/ም በደባርቅ ከተማ መሰብሰቢያ አደረሽ ስልጠና ሰጠ፡፡

የኮሌጁ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ ዶ/ር ዋሴ ጌታሁን የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ስልጠናው ደንበኞች ከዚህ ቀደም ከነበራቸው ግንዛቤና ክህሎት በተጨማሪ የተሻለ ውጤታማ ሊያደርግ የሚችል በመሆኑ በአግባቡና ስኬታማ በሆነ መልኩ ስልጠናውን እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡ ከተወሰነ ወር በኋላም ስልጠናው ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ለማወቅ ግምገማ እንደሚካሄድ አያይዘው ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው በመሰረታዊ ሂሳብ መዝገብ አያያዝና አደረጃጀት፣ በትርፍና ኪሳራ አሰላል፣ በንብረት አያያዝና ብድር አስተዳደር ጽንሰ ሃሳብ፣ በሀብት አስተዳደርና እቅድ አዘገጃጀት ላይ አተኩሮ በፕሮጀክቱ አባል መምህራን ተሰጥቷል፡፡
በመጨረሻ ስለ ሂሳብ አያያዝ፣ የብድር አወሳሰድና ሀብት አስተዳደር ጋር የተዛቡ አመለካከቶች፣ ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች፣ የወደፊት አቅጣጫዎችና በሌሎች ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ወደፊትም ከከተማ አስተዳደሩና ከአብቁተ ሀላፊዎች ጋር በቅርብ በመገናኘት ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ መ/ር ዋለልኝ አስማማው ገልፀዋል፡፡



