ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የትምህርት ፖሊሲን በተመለከተ ገለፃና ክርክር አደረጉ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ ትምህርት ኮሌጅ አዘጋጅነት ስድስተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ አስመልክቶ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን የምንጠቀምበትን የትምህርት ፖሊሲ መሰረት ያደረገ ገለፃና ክርክር ግንቦት 26/2013 ዓ.ም በማራኪ ግቢ አልሙኒየም ህንፃ መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በመርሃ ግብሩም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲያችን ከተጣለበት የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት በተጨማሪ በሃገራችን ወቅታዊ ጉዳዩች ዙሪያ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን፡፡ ከነዚህም መካከል ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ፍትሃዊና አሳታፊ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲያችን የበኩሉን ሀላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝ የገለጹት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን ዛሬ ለ2ኛ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው በሚካሄደው የተፎካካሪ ፓርቲዎች የክርክር መድረክ የያዘው ፅንሰሀሳብ የትምህርት ጉዳይ በመሆኑ አብይ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃገር የሚገነባው በፖለቲካዊ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን በትምህርት ፖሊሲም ጭምር ነው፤ ጠናካራ የትምህርት ፖሊሲ ካለ ሃገርና ትውልድ ይገነባል” ሲሉ የስነ-ትምህርት ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ክንዴ አበጀ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ክንዴ አያይዘውም ይህ መድረክ ኮሌጁ ከሚዎጣቸው ሀገራዊ ሃላፊነቶች አንዱ የትምህርት ስርአት ሀገርን የመጥቀም፣ የመገንባትና የማፍረስ ጫና እንዳለው አንስተዋል::

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአሸናፊው የፖለቲካ ፓርቲ ጋር በቅንጅት በመስራት ሀገራችን ወደተሻለ ምዕራፍ የሚያሻግር የትምህርት ፖሊሲ ቀርጸው ሊተገብሩ እንደሚገባም በእለቱ ተገኝተው የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ ገልጸዋል፡፡




