“R- markdown” የሚል የሶፍት ዌር ስልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ ድህረ ምረቃ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አዘጋጅነት “R- markdown” የሚባል በተግባር የተደገፈ የሶፍት ዌር የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ለፒ.ኤች.ዲ እና ለነባር መምህራን ከሰኔ 21-25/2013 ዓ.ም ለተከታታይ አምስት ቀናት በሳይንስ አምባ ፒ.ኤች. ዲ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተሰጥቷል፡፡

ስልጠናው የድህረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞችን በማሳደግ የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞችንን ለመቀነስ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው በመክፈቻ ንግግራቸው ተናግረዋል፡፡

በዳጉ ፕሮጀክት ድጋፍ እየተካሄደ የሚገኘው ይህ ስልጠና፣ ከአውሮፓ ሰልጥነው በመጡ የዩኒቨርሲቲው ባልደረባ በዶ/ር ብስራት ምስጋናው እና የፒ.ኤች. ዲ ተማሪ በሆኑት በአቶ ማለደ መኳንንት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ የስልጠናው ዋና አላማም ጥናትና ምርምሮችን ለመስራት መረጃ ሰብስቦ በትክክል ለመተንተን ለአቀራረብ ምቹ ለማድረግ እንዲሁም ምርምሮችን ለማሳለጥ የሚጠቅም የምርምር መረጃ ትንተና መተግበሪያን /R- markdawn/ በሚመለከት አቅምን የሚያጎለብት እንደሆነ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ የድህረ ምረቃ አስተባባሪ ዶ/ር መኩሪያው አዲስ ገልፀዋል፡፡




