የልዩ ፍላጎት እና አካቶ ትምህርት ክፍል መሰረታዊ የምልክት ቋንቋ ስልጠና በመስጠት ላይ ነው
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ-ትምህርት ኮሌጅ የልዩ ፍላጎት እና አካቶ ትምህርት ክፍል በጎንደር ዙሪያ ወረዳ በማክሰኝት ከተማ ለመምህራን፣ ለትምህርት አመራር፣ ለወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሰራተኞች እና ለወላጅ መምህራን ህብረት ከታህሳስ 8 – 10 /2013 ዓ.ም የሚቆይ ስልጠና መሰጠት ጀመረ፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ-ትምህርት ኮሌጅ የልዩ ፍላጎት እና አካቶ ትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ወንድወሰን ምትኩ እንደገለፁት መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች ከሌሎች መስማት ከሚችሉ ተማሪዎች ጋር በአንድነት ስናስተምራቸው እኩል የመጠቀም እድል ሊያገኙ አይችሉም ምክንያቱም አብዛኛው መምህራን የምልክት ቋንቋ የማስተማር ክህሎት የሌላቸው በመሆኑ ነው፡፡ ይኽም ጉዳይ ትኩረት የሚሻው በመሆኑ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ-ትምህርት ኮሌጅ የማሰልጠኛ ማንዋል በማዘጋጀት በተለያዩ አካባቢዎች ስልጠና እንዲሰጥ እያደረገ ሲሆን በማክሰኝት ከተማ የሚሰጠው ይህ ስልጠናም መሰረታዊ የሆነ የምልክት ቋንቋ መግባቢያ ምልክቶችን ለማስገንዘብ ያስችላል ብለን እናምናለን በማለት አስገንዝበዋል፡፡
ስልጠናውን በመስጠት ላይ ያሉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ-ትምህርት ኮሌጅ የልዩ ፍላጎት እና አካቶ ትምህርት ክፍል መምህርና የኮሌጁ ሪጅስትራር ኃላፊ የሆኑት አቶ ታረቀኝ አስናቀ በበኩላቸው ስልጠናው የሚሰጣቸው ከ10 ትምህርት ቤት ለመጡ መምህራን፣ለትምህርት አመራሮች፣ ለወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሰራተኞች እና ለወላጅ መምህራን ህብረት ሲሆን ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት መስማት ለተሳናቸው ተማሪዎች ተገቢ ድጋፍ በማድረግ ተማሪዎች ያለ ልዩነት መግባባት እንዲችሉ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡
የስልጠናው ተሳታፊ የሆኑትና ከጉንዲት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጡት መምህርት ሰጠችኝ አታጋልጠኝ ስልጠናው ለመምህራን መሰጠቱ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ከሚማሩ መስማት ከተሳናቸው ተማሪዎች ጋር ለመግባባት የሚያግዝ በመሆኑ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
********************************************************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ታህሳስ 8/2013 ዓ.ም







