ለንብ አናቢዎችና ግብርና ሙያተኞች ስልጠና ተሰጠ
ሀጋራችን ኢትዮጵያ ካላት የእንስሳት ሀብት ክምችት አንጻር ሲታይ የወተት፣ የስጋ፣ የእንቁላል፣ የማርና ወዘተ ምርታማነት ዝቅተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንስሳት ህክምናና ሳይንስ ኮሌጅ የግብርናውን ሴክተር ውጤታማ ለማድረግ በቴክኖሎጂ፣ በሳይንስና ምርምር የታገዙ አያሌ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም የኮሎጁ መምህራን ከዘመናዊ ንብ እርባታ ጋር በተያያዘ – “በማሸጋገርና በማባዛት ስልት የንብ ሀብትን ማሻሻል፤” በሚል ርዕስ (ከጠገዴ፣ ከአዳርቃይ፣ ከደባርቅና ከዳባት ወረዳዎች) ለተመረጡ አርሶ-አደሮችና ግብርና ሙያተኞች ከታህሳስ 16-18/2013 ዓ.ም በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ መሰብሰብያ አዳራሽ በተግባር የተደገፈ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡
የንብ ሀብት ልማትን ማሻሻል፣ ንቦችን ማባዛት እንዲሁም ከባህላዊ ወደ ዘመናዊና ሽግግር ቀፎ በማዘወር የህብረ-ንብ ቁጥርን መጨመርና ምርታማነትን ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና እንደተሰጠ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንስሳት ህክምናና ሳይንስ ኮሌጅ የዘረ-መል መምህርና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ረ/ፕሮፌሰር አዲሱ ጌጡ ገልጸውልናል፡፡
ይህ የስራ ዘርፍ (ንብ ማነብ) እንደ ሌሎች የግብርና ዘርፎች ሰፊ የቦታ ይዞታ፣ ብዙ የገንዘብና የጉልበት ወጪ እንደማይጠይቅ አስተባባሪው ገልጸው፣ አናቢዎች ይህንን እንዲረዱ ለማድረግና ያለባቸውን ክፍተት በተግባር በማሳየት ከዘርፉ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ ማስቻል የስልጠናው ዋና አላማ መሆኑን አስተባባሪው አያይዘው ተናግረዋል፡፡
አቶ ጋሻው ሞገስ ነወሪነታቸው ደባርቅ ወረዳ ድብ ባህር ቀበሌ ሲሆን ንብ በማነብ ስራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ከንብ ማነብ ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት የማያውቋቸውን በርካታ ትምህርቶችና እውቀቶች በስልጠናው እንደተገነዘቡ ገልጸዋል፡፡ ለአሰልጣኞችም ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
***************
ሀጋራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኑነት ዳይሬክቶሬት
ታህሳስ 18/2013 ዓ.ም







