በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ-ትምህርት ኮሌጅ የጃውስ ሶፍትዌር ስልጠና መስጠት ጀመረ !
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ-ትምህርት ኮሌጅ ከጎንደር ከተማ ሁሉተኛ ደረጃ ት/ቤት ለተውጣጡ የአይሲቲ መምህራን
ለአይነ-ስውራን ተማሪዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ ባለው የጃውስ ሶፍትዌር ከ10/04/2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ
ቀናት የሚቆይ ስልጠና በማራኪ ግቢ መስጠት ጀመረ ፡፡
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ-ትምህርት ኮሌጅ ዲን የሆኑት ዶ/ር ክንዴ አበጀ እንደገለፁት
የጃውስ ሶፍትዌር ስልጠና መስጠት ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት አይነ-ስውራን ተማሪዎች በትምህርት አሰጣጡ ላይ አይን
ካላቸው ተማሪዎች ጋር እኩል ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ይህን ችግር ለመቅረፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአይሲቲ
መምህራንን ማሰልጠኑ ከፍተኛ ጠቃሜታ እንዳለው በማጥናት ነበር ይህ ስልጠና እንዲዘጋጅ የተደረገው ፡፡ በመሆኑም
ሰልጣኝ መምህራን በትኩረት ትምህርቱን እንድትከታተሉ እጋብዛለሁ ሲሉ ስልጠናውን አስጀምረዋል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ-ትምህርት ኮሌጅ የጎልማሶች ትምህርትና ማህበረሰብ ልማት መምህር የሆኑት አቶ ስዩም ጥላሁን
በበኩላቸው እኔ አይነ-ስውር ብሆንም ትምህርቴን ለመማርም ሆነ አሁን ባለሁበት ሁኔታ ተማሪዎችን ለማስተማር የጀውስ
ሶፍትዌር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ሲሉ ያስረዱ ሲሆን ሌላው አይነ-ስውር የሆኑትና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሶሻል ሳይንስና
ሂዩማኒቲ ኮሌጅ የስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር መምህር የሆኑት አቶ ታደለ ቢክስ በበኩላቸው አይነ ስውራን የሰው ድጋፍን
በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈልጉ ቢሆንም ስለጃውስ በቂ እውቀት ያለው አይነ-ስውር ግን ሰማኒያ ከመቶ ያህል በትምህርት
ጉዳዮችና ጥናትና ምርምር ለማድረግ ተጠቃሚ መሆን ያስችለዋል ሲሉ አስረድተዋል ፡፡
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
******************************
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ታህሳስ 13/2013 ዓ.ም







