የተማሪዎች ህብረት ምርጫ በ21/02/2008 ዓ.ም
የተማሪዎች ህብረት የምርጫ ፕሮግራምን በንግግር የከፈቱት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳንት ተወካይ በንግግራቸው ምርጫ የምታከናዉኑ ተማሪዎች እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዉ የተናገሩ ሲሆን የተማሪዎች ህብረት ሚና በዩኒቨርሲቲው ዉስጥ ከፍተኛ በመሆኑ መራጮች ትኩረት ሰጥታችሁ መምረጥ ይገባችኋል ብለዋል፡፡

ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳንት ተወካይ
የምትመረጡት የተማሪዎች ህብረት ተወካዮች ለተማሪው መብት ብቻ ሳይሆን ተማሪዎችም የዩኒቨርሲቲውን ህግና ደንብ እንዲያከብሩ እንድታደርጉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ለተማሪዎች ህብረት የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ከጎናችሁ በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

የተማሪዎች ህብረት ምርጫ ዋና ዓላማ ተማሪዎች ተወካዮቻቸዉን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መምረጥ ሲሆን የሚመረጡ የተማሪ ተወካዮች የአገልግሎት አሰጣጥንና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን በመከታተል የተማሪዎችን መብት ማስጠበቅ ቀዳሚዉ ተግባራቸዉ ሲሆን ለዩኒቨርሲቲው ህግና ስርዓት መከበርና ለመማር ማስተማሩ መልካም ውጤት ተገቢ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው በምርጫ ስርዓቱ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
የአስተዳደር ም/ፕሬዚዳንቱ አቶ ሰለሞን አብርሃ በበኩላቸዉ የ2008 ዓ.ም የተማሪዎች ህብረት ምርጫ ማስፈፀሚያ ዕቅድን በሰፊው አቅርበዋል

የምርጫ መስፈርቱም በከፊል እነዚህን ያካትታል
- በዲሲፒሊን የታነፀ(ች)
- ከአጉል ሱስ ነፃ የሆኑ
- የተጣለባቸዉን ኃላፊነት በአግባቡ የሚወጡ
- በሁለንተናዊ መልኩ ዓርዓያ የሆነ ዉጤታቸዉም ከ2.5 በላይ የሆኑ የሚሉ ሲሆኑ እነዚህ ተመራጮች የ21 ሽህ ተማሪዎችን ድምፅ ወክለዉ ስለሚይዙ ምርጫዉ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ በጥንቃቄ መከናወን ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አቶ አንተነህ ደመቀ የተማሪዎች ዲን በበኩላቸዉ ለተመራጮች ሁለንተናዊ ድጋፍ የሚደረግ ሲሆን ተማሪዎች ለትምህርት ጥራትና ለዩኒቨርሲቲው ጤናማ የትምህርት አሰጣጥ ክፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
//ሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት//

