ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህንድ ከሚገኘው ፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ ፓቲላ(ፒዩፒ) ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረመ
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማይቻለውን እንዲቻል እያደረገ ነው!

ከአምስቱ ስትራቴጂካዊ አብይ ርእሰ ጉዳዮች አንዱ በሆነው ‘አለማቀፋዊነት’መነሻ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከበርካታ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር የትብብር ስምምነቶችን በአለማቀፍ ደረጃ እያካሄደ ነው፡፡ለአብነትም ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ ከፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ ጋር አንድ ስምምነት የተፈራረመ ሲሆን ስምምነቱን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት፣የተከበሩ ዶ/ር አስራት አጸደወይንና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ዩኒቨርሲቲውን ወክለው ወደ ህንድ በመጓዝ ከፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ ፓቲላ አቻቸው ከም/ቻንስለር ፣የተከበሩ ዶ/ር ጃስፓልሲንግ ጋር ተለይተው በታቀዱ የትብብር ስምምነቶች ና ቀጣይ በሚስፋፉ እቅዶች ዙሪያ የካቲት 29/2008 ዓ.ም መክረዋል፡፡

ይህ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፒኤች ዲ ትምህርታቸውን በሚከታተሉ ሙህራን ማለትም በአቶ ሙሉ አደሬ፣አቶ ተሻለ ብርሃኑ እና አቶ ስለሽ ግርማ አነሳሽነት የተጀመረው አርአያነት ያለው የወዳጅነት ስምምነት የዩኒቨርሲቲው ስታፍ አባላት የእናት ተቋማቸውን አለማቀፋዊነት ለማሳደግ ያላቸውን ተነሳሽነት ና ተሳትፎ ሚያሳይ እንደመሆኑ መጠን በጣም የሚበረታታና ለሌሎችም ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ተግባር ነው፡፡
በሁለቱ ተቋማት መካከል ሁለት አበይት የትብብር ስምምነቶች የተፈረሙ ሲሆን ስምምነቶቹ ከሚያካትቷቸው ጉዳዮች መካከልም፡ በማኔጅመንት ኢኮኖሚክስ ቱሪዝምና ፋይናንስ ፒኤች ዲ የትምሀርት ይዘቶችን በማበልጸግ እንዲሁም በማስተማርና ጥናትና ምርምር ላይ በጋራ መስራት የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ስምምነቱን ወደ ተግባር ለመቀየር ሁለቱም አካላት የመነሻ የውይይት መድረክ በኢትዮጵያ እንደሚዩዙና ስለ ዝርዝር አፈጻጸሙ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች ጋር እንደሚመክሩ ተገልጧል፡፡ ይህን ተግባር ለማስፈጸምም በአካዳሚክ ጉዳዮች ፕሮፌሰር ኤ.ኤስ ቻውላ እና ስምምነቱን በኃላፊነት በፈረሙት ፕሮፌሰር ናቭጆት ካውር የሚመራ ፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ ፓቲላን የሚወክል ቡድን ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንደሚመጣ ታቅዷል፡፡የሀለቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ፕ/ር ናቭጆት ካውር በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሚኖራቸው ቆይታ በተቋማቸው ያለውን የፒ ኤች ዲ ፕሮግራምና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስታፍ አባላት ገለጻ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
የሁለቱም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተዎካዮች በስፋት እንደተዎያዩባቸው ለወደፊት ትኩረት ከሚሰጡባቸው ሶስት የትብብር አቅጣጫዎች መካከል የቱሪዝምተሳትፎ ማሳደግ ፣አጫጭርና ረዣዥም የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እንዶሁም የሃብት መጋራትና ማንቀሳቀስ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን የተመራው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ልዑካን ቡድን በፒዩፒ የፒ ኤች ዲግሪ ትምህርታቸውን ከሚከታተሉ የጎንደር የኒቨርሲቲ ስታፍ አባላትን አግኝተው ስለትምህርትና አኗኗር ሁኔታቸው ምን እንደ ሚመስል የተወያዩ ሲሆን አንዳንድ ችግሮችን በተመለከተ በአስተናጋጁ ዩኒቨርሲቲ ከሚመለከታቸው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን ለመፍታት መክረዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ “አንድ መጽሃፍ ለዩኒቨርሲቲየ ቤተ መጽሀፍት “ በሚል ዩኒቨርሲቲያቸውን በመጽሃፍ ልገሳ ለመደገፍ ታልሞ በቋቋመው ግብረ ሰናይ ቡድን ደማቅ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን በህንድ ቆይታቸውም በፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ ና በከተማዋ ያለውን የመሰረተ ልማት እንቅስቃሴ ማለትም የዩኒቨርሲቲውን ውብ ቤተ ቤተመጽሃፍት ፣የተማሪዎች መመገቢያና መዝናኛ ሎጅ፣የስፖርት ማዘውተሪያ ፣ጂም እና ሌሎችም አካባቢዎች ጎብኝተዋል፡፡
ትርጉም፡ደስታው ዋኘው

