የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ አዉደ ርዕይ አቀረበ
25ኛዉን የግንቦት 20 የብር እዮቤልዮ የድል በዓልን ምክንያት በማደረግ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎቹን፣ የምርምር ግኝቶቹንና የማህብረሰብ አገልግሎቶችን በቦታዉ በመገኘት ከግንቦት 15- 18/2008 ዓ.ም ለህዝብ ይፋ አደረገ፡፡

ለተከታታይ አራት ቀናት የዩኒቨርሲቲዉን ስራዎች በትጋትና በሚያምር ገለፃ ለበርካታ ጎብኝዎች ሲያስታዋዉቁና ሲያብራሩ የነበሩት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአለም አቀፈፍ ግንኙነት የቡድን መሪ አቶ ኤልያስ መንበር፣ የእንደስትሪ ትስስርና ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን መስፍን፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጤናና ህክምና ኮሌጅ የመስክ የቡድን ስልጠና(TTP) አስተባባሪ የሆኑት አቶ ጌታ አስራደ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል ሃላፊ አቶ ይልቃል ሙሉአለም፣ በአይሲቲ ክፍል የኢ- ለርኒንግ (e-learning) ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ወንድምአገኝ አላምረዉ ናቸዉ፡፡
ዩኒቨርሲቲው በአውደ ርዕይዉ የህብረተሰቡን ችግር በመፍታት ለሀገር እድገት ትልቅ ድርሻ እያበረከተ እንዳለ የሚያሳዩ ስራወቹን አቅርቧል፡- በፀሀይ ብርሃን የምትሰራ ባጃጅ፣ በባዮ ጋዝ የሚሰራ መኪና፣ የእንቦጭ(የዉሃ ላይ) አረምን በማጨድና እንዳይራባ በመቀቀል ማስወገድ የሚችል መርከብ፣ የመኪናዎች እንቅስቃሴ መከታተያ ሶፍትዌር፣ የደሮ እንቁላሎችን መፈልፈል የሚችል ኢንኩቤተር፣ የሳንባ ካንሰርን መለየት የሚችል መሳሪያ፣ ድንችና ካሮት መላጥ የሚችል መሳሪያ እና ከወዳደቁ ወረቀቶችና ከእንጨት ፍቅፋቂ ክሰልን የሚተኩ ብርኬቶች ማምረት የሚችሉ ማሽኖች ከቴክኖሎጂ ዉጤቶች ለህዝብ እይታ የቀረቡ ናቸዉ፡፡ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች ከመመረቃቸዉ በፊት የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት እንደመለማመጃ የሚጠቀሙበትን የመስክ የቡድን ስልጠና (team training pragramm/TTp) ስራዎች በጤናዉ ዘርፍ በአዉደ ርዕይዉ የቀረቡ ነበሩ፡፡ ከደሮ ጽዳጅ፣ ከቦቆሎና ከዱቤ ከተባለ ጥቁር አፈር የተገኙት ነዳጆች እንዲሁም ከዳጉሳ ዝርያ የተጠመቀ ቢራ በሚሊኒየም አዳራሽ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በኩል ለእይታ ከቀረቡት የምርምር ዉጤቶች መካከል የሚጠቀሱ ሲሆኑ ሁሉም በጎብኝዎች ዘንድ እጅግ በጣም አድናቆትን ያገኙ ሁነዋል፡፡

ሀገሪቱ ከድህነት ለመላቀቅ ለምታደርገዉ ጉዞ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትልቅ ሀላፊነት እንዳለባቸዉ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም አንጋፋዉ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለበርካታ ዓመታት ሀገራዊ ድርሻዉን እየተወጣ ይገኛል፡፡ በዚህም የተነሳ ለስድስት አስርት ዓመታት ዩኒቨርሲቲዉ ለሀገር ያበረከታቸዉን አስተዋፆዎች የተረዱት በሚሊኒየም አዳራሽ የተገኙ የተለያዩ የሀገሪቱ ህዝቦች ለተቋሙ ያላቸዉን ከፍተኛ አክብሮት ገልጸዋል፡፡
ከአስተያየት ሰጭዎች መካከል የቀድሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪና አሁን የንግድ ባንክ ሰራተኛ የሆነዉ ወጣት ሙሉቀን አበበ ባገኘዉ አጋጣሚ የዩኒቨርሲቲዉን ትምህርት አሰጣጥ በማድነቅና በአዉደ ርዕይዉ በተመለከተዉ ነገር እጅግ በመደሰቱ የተነሳ የዩኒቨርሲቲዉ ሙሩቅ መሆኑ እንደሚያኮራዉ ተናግሯል፡
የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ጥላነሽ ደርበዉ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከዉጭ ተመርተዉ የሚመጡ ነዳጆችንና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ዉጤቶችን በሀገር ዉስጥ ለማምረት በመቻሉ የሀገር ኩራት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነዉ ብለዋል፡፡
አቶ ሀብታሙ ዮርሴ የአትዮጲያ ዜና አገልግሎት ፕሮዳክሽን አዘጋጅ ያዩት የቴክኖሎጅና የምርምር ፈጠራ ስራወች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በመሆናቸዉ በዩኒቨርሲቲዉ መኩራታቸዉን ገልጸዉ ለዎደፊትም ከዩኒቨርሲቲዉ ጋር አብረዉ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸዉ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
የዉጭ ጉዳይ ሚኒስተር አባል የሆኑት አቶ በድሉ በሻዉ በአዉደ ርዕይዉ የቀረቡት የዩኒቨርሲቲዉ ስራወች አገራችን የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ የሚያሳይና የወደፊት የሀገሪቱን ዕድገት ሊያመላክቱ የሚችሉ ስራወች በዩኒቨርሲቲዉ እየተሰሩ በመሆናቸዉ ደስታቸዉ ወሰን እንደሌለዉ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም በዝግጅቱ ላይ የጎንደር ዩኒቨርሲቲን በመዎከል አዳዲስ የቴክኖሎጅዎችና የምርምር ዉጤቶችን በማስተዋወቅና ገለፃ በማድረግ የተሳተፉት የህዝብና አለምአቀፍ ግንኙነት አባላትም የታታሪዉ ዩኒቨርሲቲ አባል በመሆናቸዉ እጅግ ከፍተኛ ኩራት እንደሚሰማቸዉ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡-አምሳሉ ግዛቸው
አርታኢ፡ ደምሴ ደስታ

