የህክምናና ጤና ሳይንስ ተመራቂ ተማሪዎች የቲቲፒ ፕሮጀክቶቻቸዉን አስመረቁ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ4ኛ እና የ5ኛ አመት የህክምና ተማሪዎች በመጀመሪያዉ ዙር ከየካቲት 12 እስከ መጋቢት 27/2008 ዓ.ም በሁለተኛዉ ዙር ከሚዚያ 7 እስከ ከግንቦት 27/2008 ዓ.ም ድረስ በነበረዉ የመስክ የቡድን ስልጠና መርሀ ግብር በአዘዞ፣ በጎንደር-ቀበሌ 18፣ በቆላድባ፣ በዳባት፣ በደባርቅ፣ በአዲስዘመን እና በወረታ ከተሞች የሰሯቸዉን የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ከመጋቢት 21 አስከ መጋቢት 25/2008 ዓ.ም እንዲሁም ከግንቦት 25 እስከ 27/2008 ዓ.ም ለተጠቃሚዉ በማሰረከብ አስመረቁ፡፡

መምህር ጌታ አስራደ የTTP አስተባባሪ
ተማሪዎች ከየትምህረት ከፍሉ ተወጣጥተዉ በቡድን በቡድን በመደራጀት የካቲት 12/2008 ዓ.ም ወደ ተመደቡባቸዉ ከተሞች በመሄድ የህብረተሰቡን ችግሮች በማጥናትና በመለየት፣ ከአካባቢዉ ነዋሪዎችና ከሚመለከታቸዉ ሀላፊዎች ጋር በመወያት እና በተግባራት ላይ የጋራ እዉቅና ፈጥረዉ በቁርጠኝነት ስራቸዉን እንደጀመሩ የቲቲፒዉ አሰተባባሪ አቶ ጌታ አስራደ ገልጸዋል፡፡ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ኢኒስቲቲዉት ዳይሬክተር ዶ/ር አበባዉ ገበየሁ በመጀመሪያዉ ዙር የTTP ፕሮግም በዳባትና በደባርቅ ከተማዎች ተገኝተዉ ተማሪዎች የሰሩትን ህብረተሰብ አቀፍ ፕሮጀክቶችን ሲመርቁ እንደተነገሩት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከሌሎች የኢትዮጵያ የህክምና ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የሚለየዉ ተማሪዎች ተመርቀዉ መደበኛ ስራቸዉን ከመጀመራቸዉ ከአንድ አመት ወይም ከጥቂት ወራት አስቀድሞ ህብረተሰቡን ከቀየዉ ድረስ በመሄድ በቀጥታ በማግኘት፣ ያለበትን መሰረታዊ ችግሮችን በማጥናትና በመለየት በፕሮጀክቶቻቸዉ መፍታት መቻላቸዉ ነዉ ብለዎል፡፡
በሂደቱም ወቅት ተማሪዎች የቲቲፒ ቢሮ ባዘጋጃቸዉ የዳሰሳ ጥናት መጠይቆች መሰረት በየተመደቡበት አካባቢ የሚኖረዉን ማህበረሰብ ችግር በመጠየቅና በማየት ለይተዎል፡፡ ችግሮችን ከለዩ በኋላ ሊሰሩት ስላቀዱት ፕሮጀከትና ተግባራት ለአጋር አካላት፣ ለበጎአድራጊ ድርጅቶች፣ ተባባሪ ለሆኑ ግለሰቦች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ደርጅቶች በማቀረብ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችንና የግንባታ ቦታዎችን አግኝተዎል፡፡ እነዚህን ቁሳቁሶች በማሟላት ፕሮጀክቶቻቸዉን ለማሳካት ብዙ ዉጣ ዉርዶች እንዳጋጠሟቸዉ የየመስኩ ቡድን መሪዎች በምረቃዉ ስነስራዓት ለነበረዉ ታዳሚ አስረድተዋል፡፡
ተማሪዎች በቆይባቸዉ ቀናት ዉስጥ በማረሚያ ቤቶች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ጣቢያዎች፣ በሀይማኖት ተቋማት እና ሰዎች በጋራ በሚኖሩባቸዉ አንዳንድ አካባቢዎች የቧንቧ ዉሃ፣ የደረቅና የፈሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ጉድጓዶች፣ የሻወር ቤቶች፣ መጸዳጃ ቤቶች፣የምግብ መመገቢያ አዳራሽ፣ የልብስ ማጠቢያ ገንዳዎች፣ የችግኝ ተከላ፣ የአካባቢ ጽዳት ሰራና የማስተማር ተግባራትን፣ህ/ሰቡን በማነቃነቅ የደም ልገሳ አገልግሎት ማድረግ ወዘተ በኅብረተሰብ አቀፍ ፕሮጀክታቸዉ ካከናዋኗቸዉ ተግባራት መካከል ዋና ዋናዋቹ ናቸዉ፡፡
እንዚህን ተግባራት በ45 ቀናት ዉስጥ ለማከናወን በየቡድኑ የነበሩ እያንዳንዱ አባላት ደንጋይ፣አሽዋ፣ስሚንቶ ቆርቆሮና እንጨት ተሸክመዋል፣ ድንጋይ ፈልጠዋል፣ ጉድጓድ ቆፍረዋል፣ እረጅ አካል ፍለጋ ከመስሪያ ቤት መስሪያ ቤት፣ ከከተማ ከተማ፣ ከወረዳ ወረዳ ፀሐይና በርዱ ሳያግዳቸዉ ሌት ተቀን ዙረዋል፡፡ ተመላልሰዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ ተማሪዎች ለአካባቢዉ አዲስና እንግዳ ቢሆኑም የእንግዳነትና የባይተዋርነት ሰሜት ሳይሰማቸዉ በአጭር ጊዜ ለማህበረሰቡ እጅግ ጠቃሚ ተግባራትን ማከናወን ችለዋል፡፡ ህሙማንን ከህክምና ባለሙያዎች ጋር በመሆን አክመዋል፡፡
የመጀመሪያ ዙር የቡድን ሰልጣኝ ተማሪዎች ባጠቃላይ በጎንደር ቀበሌ 18 አንድ ሻወር ቤት፣ አንድ ባለ ሦስት ገንዳ የልበስ ማጠቢያ፣500 ሊትር የሚይዝ አንድ የመጠጥ ዉሃ ታንከር፣ በአበራ ጊወረጊስ አጸደ ህፃናት ትምርት ቤት ለመምህራንና ለተማሪዎች የማረፊያና የመመገቢያ አንድ አዳራሽ እና በማራኪ ጤና ጣቢያ ባለ ላሜራ ክዳን የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ጉድጓድ ከሰሯቸዉ ስራዎች መካከል ይገኙበታል፡፡

ባዘዞ ቀበሌ 20 በአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ለሚገኙ ታራሚዎች ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በእርዳታ በተገኘ 3,500 ሊትር ዉሃ የሚይዝ ታንክር በማዘጋጀት የዉሃ እጥረቱን በአጭር ጊዜ እንዲቀረፍ አድርገዋል፡፡ 500 ሊትር ዉሃ የሚይዝ ታንከር አድሰዉም ለታራሚዎች ከመፀዳጃ ቤት በፊትና በኃላ እጆቻቸዉን እንዲታጠቡ አስችለዋል፡፡ አንድ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ጉድጓድ ቆፍረዋል፡፡ እነዚህ ታታሪ የህክምና ተማሪዎች የፈሳሽ ቆሻሻን ማስረጊያ ዘመናዊ ገንዳ ለታራሚዎች ከክፍላቸዉ ዉስጥ ሰርተዉላቸዎል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በዚህ ቀበሌ በቀጠና 1፣2፣3 እና 4 የሚኖረዉ ማህበረሰብ የጋራ የሆነ መጸዳጃ ቤት ቢኖረዉም ሀላፊነት በጎደለዉ መንገድ ለአጭር ጊዚያት ሲገለገሉበት የነበረና በሀላፊነት የተወከለ ሰዉ ባለመኖሩ በመጸዳጃ ቤቶች ዉስጥና ዉጭ ቆሻሻ ሲጣልበት የኖረና በቆሻሻ ክምር ተሞልቶ ህብረተሰቡ የትም ቦታ እንዲጸዳዳ ምከንያት በመሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ሰዎች በተቅማጥና በትዉኪያ ሲጠቁ መሆራቸዉን የአዘዞ ሳይት የቲቲፒ ቡደን መሪ የሆነዉ ተማሪ አለሙ ኖራ በጉብኝቱ ወቅት ለተገኘዉ ታዳሚ ገለጻል፡፡ የዛምራ ኮንስትራክሽን ባደረገቸዉ የቡል ዶዘር እገዛ ለአመታት የተከማቸዉን የቆሻሻ ክመር ከቦታዉ በማንሳት አራት ቢያጆ አፈር በሲኖትራከ መኪና በማስደፋት እና በመደልደል የመጸዳጃ ቤቶችን አካባቢ ንጹህ አድርገዎል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ከአካባቢዉ ኑዋሪ ጋር በመሆን በቀጠና 1፣2 እና3 የሚገኙ እያንዳንዳቸዉ ስድት ስድስት ክፍሎች ያላቸዉን ሶስት መጸዳጃ ቤቶች ከተለያዩ ግለሰቦች በተገኘ ጠቅላላ ድምር 74,000 ብር በማዉጣት አድሰዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የአዘዞ ኑዋሪ የሆኑት አቶ ዳኘ ንጉሴ ስለተደረገላቸዉ መልካም ስራ ሲገልጹ ‹‹የወለዱት ይወልዳል›› በማለት ልባዊ ምስጋናቸዉን ለተማሪዋችና ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ገልጸዋል፡፡
ቆላድባ ከተማ የወጡ በተግባር ላይ የሚሰለጥኑ የቡድኑ ተማሪዎች በቆላድባ ፖሊስ ጣቢያ አንድ የደረቅ ቆሻሻ ማቃጠያ ጉድጓድ ቆፍረዋል፤ ወርልድ ቨዠን ባደረገላቸዉ ትብብር እያንዳንዳቸዉ ሁለት ቀዳዳ ወይም መቀመጫ ያላቸዉ ሁለት መጸዳጃ ቤቶች፣ በቆላድባ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ባለ ስድት ፎሴት አንድ ቧንቧ፣ በቆላድባ ጣና ሐይቅ አፀደ ህፃናት ት/ቤት ባለ ሁለት ፎሴት አንድ ቧንቧ፣ በቆላድባ ፖሊስ ጣቢያ ባለ 10 መቀመጫ እንድ መጸዳጃ ቤት ሙሉ የሆነ እደሳ አድርገዋል፡፡

ዶ/ር ይንገስ አለሙ የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዚዳንት በቆላድባ የቲቲፒ ፕጀክቶችን ሲመረቁ
በቆላድባ ጣና ሐይቅ አፀደ መዋለ ህፃናት ባለ አራት መቀመጫ አንድ መጸዳጃ ቤት እንዲሁም ሁለት የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጅ ሰርተዉ ለተጠቃሚዉ ህብረተሰብ አስረከበዎል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአንጋፋዉ የቆላድባ ጤና ጣቢያ የፈሳሻ ማጠራቀሚያ (ሴፕቲ ታንከር) ሰርተዋል፡፡
በዳባት ከተማ ዳባት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለ ስድስት ፎሴት አንድ ቧንቧ፣በዳባት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለ ስድስት ፎሴት አንድ ቧንቧ በመሰራት ከ5000 በላይ ለሚሆኑ ለትምረት ቤቱ ተማሪዎች፣ ለመምህራንና ለአስተዳደር ሰራተኞች ንጹህ ዉሃ እንዲያገኙ አድርገዋ፡፡ ሶስት መጸዳጃ ቤቶች አንዱ ባለ አራት መቀመጫ ሁለተኛዉ ባለ ስድሰት መቀመጫ፣ሶስተኛዉ ባለ ሶስት መቀመጫ ሰርተዉ ለተጠቃሚዉ አስረከበዋል፡፡ አራት ከፍል ያለዉ ሻወር ገንብተዉ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ለዳባት ማረሚያ ቤት ታራሚዎች አገልገሎት እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡ አንድ የደረቅ ቆሻሻ ጉድጓድ ገንብተዋል፡፡

በዳባት ከተማ በቲቲፒ ፕሮገራም የተሰሩ ፕጀክቶች ሲመረቁ የሚያሳይ ከፊል ስዕላዊ መግለጫ
በደባርቅ ከተማ ሁለት መጸዳጃ ቤት፣ በደባረቅ አንደኛ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት አንድ መጸዳጃ ቤት እና በሚካኤል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንድ መጸዳጃ ቤት፣በደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ባለ ስድስት መቀመጫ አንድ መጸዳጃ ቤት ሲገነቡ፣ አንድ የደረቅ ቆሻሻ ማሰወገጃ ጥልቅ ጉድጓድ፣420 ለሚሆኑ ታራሚዎች ባለሁለት አፍ ሻዋር በማደስ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ እንዲሁም በደባርቅ ጤና ጣቢያ አንድ የእንግዴ ልጅ ማስወገጃ ጥልቅ ጉድጓድ ቆፍረዉ ለአገልግሎት አብቅተዋል፡፡

ዶ/ር ሲሳይ ይፍሩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን በወረታና በአዲስ ዘመን የቲቲፒ ፕጀክቶችን ሲመረቁ
በወረታ ከተማ በዱድመኝ አንደኛ ደረጃ ትምርት ቤት እና በወረታ ሁለተኛና መሰናዶ ት/ቤት እያንዳንዳቸዉ ስድስት መቀመጫ ያላቸዉ ሁለት መጸዳጃ ቤቶች፣ በወረታ ቀበሌ ሶስት አራት መቀመጫ ያለዉ አንድ መጸዳጃ ቤት፣በወረታ (በጓያ) አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ሶስት ፎሴት ያለዉ 6000 ሊትር ዉሃ የሚይዝ አዲስ ታንከር ለ3300 ተማሪዎች እና 150 መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች የንጹህ ዉሃ አቀርቦት እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡ በአዲስ ዘመን አንድ መጸዳጃ ቤት፣ አንድ የጉድጓድ እጅ ፓምፕ የመጠጥ ዉሃ፣ የደረቅ ማስወገጃ ጉደጓዶች በመስራት ለማህበረሰቡ አስረክበዋል፡፡
በአጠቃላይ እነዚህ ተመራቂ የህክምና ተማሪዎች በሁለቱ የቡድን የመስክ ላይ ስልጣና (TTP) 52 አነስተኛ ፕጀክቶች ተሰርተዉ ለአካባቢዉ ማህበረሰብ አገልገሎት እንዲሰጡ አደርገዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ይላቅ አለባቸዉ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ከፍተኛ ሪፖርተር
አርታኢ፡ ደምሴ ደስታ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር

