የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 2ኛዉን አመታዊ ተቋማዊ የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስ አካሄደ፡፡
በሀገር አቀፍ በዩኒቨርሰቲ ደረጃ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንደተጀመረ የሚነገርለት የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስ ከዚህ በፊት ዩኒቨርሲቲዉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁለት ጊዜ ካዘጋጀ በኋላ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ከተቋሙ ያገኙትን ልምድ በመጠቀም በወረፋ በየአመቱ ሀገራዊ የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስ በማዘጋጀት እንዲካሄድ ያደርጋሉ፡፡ በመሆኑም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ራሱን የቻለ ተቋማዊ የሆነ አመታዊ የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስ ማካሄድ በተቋሙ የሚሰጠዉን ትምህርት ይበልጥ ደረጃዉን የጠበቀ እንዲሆንና የተቋሙ ማህበረሰብ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት አንዲሰጡ በማስቻል የአጠቃላይ የተቋሙን ሁለንተናዊ አቋም በሁሉም ዘርፍ ጥራቱንና ደረጃዉን ይበልጥ በማሳደግ ሀገራዊ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ለማስቻል በየአመቱ ተቋማዊ የሆነ የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስ በዩኒቨርሲቲዉ የትምህርት ጥራትና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት አማካኝነት ያካሂዳል፡፡
በተመሳሳይ በዚህ ዓመት ታህሳስ 21-22/2009 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲዉ ለ2ተኛ ጊዜ “Enhancing quality of education through system transformation” በሚል የዓመቱ መሪ ቃል የሚካሄደዉን አመታዊ ተቋማዊ የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስ የትምህርት ሚኒስቴር ሚንስተር ድኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ፣ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ጀነራል ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋየ ሙህየ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕረዝዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ም/ፕረዝዳንቶችና የዩኒቨርሲቲዉ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲዉ ሁሉም መምህራን እና የተማሪዎች የተለያዩ አደረጃጀት ተወካዮች የተገኙ ሲሆን በሀገሪቱ ከሚገኙ ከሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎችና ከተለያዩ ተቋማት ጥሪ ተደርጎላቸዉ የመጡ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ምሁራን የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡

በመጀመሪያ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ለተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡ ዶ/ር ደሳለኝ በንግግራቸዉ ዩኒቨርሲቲዉ እያከናወናቸዉ ያሉትን አብይ ተግባራትን አንስተዋል፡፡ ለአብነት ያክል በ2008ዓ.ም ዩኒቨርሲቲዉ በኢትዮጵያ የጥራት ደረጃዎች ኤጀንሲ የ1ኛ ደረጃ የጥራት ተሸላሚ መሆኑ፤ ዩኒቨርሲቲዉ በ2008 በጀት ዓመት በሃገሪቱ ከሚገኙ ነባር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመወዳደር የ1ኛ ደረጃ ተሸላሚ መሆኑ፤ ዩኒቨርሲቲዉ በአይሲቲ ቴክኖሎጂ እያሳየ ያለዉ እምርታ፤ በህክምናዉ ዘርፍ ዩኒቨርሲቲዉ እየተገበረ ያለዉ አዳዲስ አሰራርና መልካም አፈጻጸም፤ በኢንጅነሪንግ ኢንስቲትዩት እየተሟሉ ያሉ አዳዲስ ዎርክሾፖች እና ዩኒቨርሲቲዉ እያሳየ ያለዉ አጠቃላይ የመሰረተ ልማት መሟላት፤ ዩኒቨርሲቲዉ በሚያከናዉናቸዉ የተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች፣ ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናቶችን በማካሄድ እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ዩኒቨርሲቲዉ ዉጤታማ ዓመታትን ማሳለፉን አውስተዉ ለተገኘዉም ዉጤት የተቋሙን ማህበረሰብ እና አጋር አካላትን አመስግነዋል፡፡ በተመሳሳይ የተገኘዉንም አመርቂ ዉጤት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ጠንክሮ በመስራት በላቀ ሁኔታ ማስቀጠል እንደሚገባ አበክረዉ ገልፀዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ድኤታ ዶ/ር ሳሞኤል ክፍሌ ኮንፈረንሱን በንግግር ሲከፍቱ የትምህረት ጥራት ኮንፈረንስ በሀገር አቀፍ ደረጃ መካሄድ የጀመረዉ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቢሆንም አሁን ሌሎች የመንግስትና የግል የኒቨርሲቲዎች የጎንደር ዩኒቨርሲቲን መልካም ተሞክሮ በመከተል በየ አመቱ በማካሄድ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ አያይዘዉም አሁን ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ “Enhancing quality of education through system transformation” በሚል የዓመቱ መሪ ቃል ዩኒቨርሲዉ የሚያካሂደዉን ተቋማዊ አመታዊ የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስ በመክፈቻ ንግግር እንዲከፍቱ በመጋበዛቸዉ ደስታቸዉን ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ሳሙኤል ከትምህርት ጋር የተያያዙ ተቋማዊ ብሎም ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት መሰል ኮንፈረንሶች አዎንታዊ ሚና እናዳላቸዉ በመግለጽ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አሁንም ቢሆን ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮ ሊሆኑ የሚችሉ አዳዲስ ግኝቶችንና አሰራሮችን በማፍለቅ የአራያነቱን ሚና እንደሚያስቀጥል ሙሉ እምነታቸዉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በመቀጠል የከፈተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ጀኔራል ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋየ ሙህየ በዕለቱ ኮንፈረንስ ርዕሰ-ጉዳይ ዙሪያ ቁልፍ ንግግር(keynote speech) አድርገዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋየ ከ7 ዓመት በፊት የዩኒቨርሲቲዉ የአስተዳደር ም/ፕረዝዳንት በመሆን መስራታቸዉን አዉስተዉ አሁን ዩኒቨርሲቲዉ ያለበት አጠቃላይ አቋም በእጅጉ እንዳስደነቃቸዉ የገለጹ ሲሆን በ2008 ዓ.ም ለተገኘዉ የቀዳሚነት ዉጤትና ዩኒቨርሲቲዉ ላሳየዉ አስደናቂ እድገት ለሁሉም የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ ያላቸዉን አከብሮት ገልፀዉ ማህበረሰቡም ይበልጥ በመትጋት አሁን ያለዉን ተነሳሽነት ማስቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የአድስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፕ/ር እንደሻዉ በቀለ የትምህርት ጥራትን አስመልክቶ በተጨማሪም ቁልፍ ንግግር አድርገዋል፡፡ ፕ/ር እንደሻዉ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ከመማር ማስተማሩ በተጨማሪ ለአጠቃላይ የሃገር እድገት በሁሉም ዘርፍ አዉንታዊ ሚና እንዳለዉ ገልጸዋል፡፡

በመቀጠል የዩኒቨርሲቲዉን ፕረዝዳንት ደ/ር ደሳለኝ እንዲሁም የእለቱን ኮንፈረንስ ፕሮግራም የመሩትን የዩኒቨርሲቲዉ የትምህርት ጥራትና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ደይሬክተር የሆኑትን ወ/ሪት ሃና ሽዋ ሞላቶትን ጨምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ዩነቨርሰቲዎች በመጡ ምሁራን ከትምህርት ጥራት ጋር ግንኙነት ያላቸዉ ጥናታዊ ጹሁፎችን ያቀረቡ ሲሆን በቀረቡ ጥናቶች ላይ ጥልቅ ዉይይት ተካሂዶባቸዋል ይበጃሉ የተባሉ ቀጣይ አቅጣጫዎችም ላይ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በመጨረሻም ከመደበኛዉ ስራቸዉ ዉጭ የተሰጣቸዉን ሙያዊ ሀላፊነት በላቀ ሁኔታ በመወጣት ብሎም የተለያዩ የፕሮጀክት እና የምርምር ስራዎችን በመቅረጽና በመተግበር ለፕሮጀክት የሚሆን ስፖንሰር በማፈላለግ በርከት ያለ ስራ ማስኬጃ ገንዘብ ያስገኙ እና በዉጤታማ የጥናትና የምርምር ስራቸዉ ዩኒቨርሲቲዉን በበጎ ያስጠሩ 14 የዩኒቨርሲቲዉ አባላት ላበረከቱት ላቅ ያለ አስተዋጾ ዩኒቨርሲቲዉ ለ6ቱ ላፕቶፕ፣ 10 ግራም የወርቅ ሀብል ለእያንዳንዳቸዉ፣ መዳሊያ እና የእዉቅና ሰርቲፊኬት ሽልማቶችን የሰጠ ሲሆን ለቀሩት ለ8ቱ ደግሞ የ10 ግራም የወርቅ ሀብል ለእያንዳንዳቸዉ፣ የእዉቅና ሰርቲፊኬት በሽልማት መልክ ተበርክቶላቸዋል፡፡

የህ/ዓ/አ/ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

