አዝናኝ ጥበባዊ ድግስ በማራኪ ግቢ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ስር የሚገኘው ቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል አዝናኝ የኪነ- ጥበብ ዝግጅትና ሰሚናር አካሄደ፡፡ ዝግጅቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ደ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ ተወዳጇ አርቲስት መሰረት ህይወት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም የኮሌጁ መምህራንና ተማሪዎች በተገኘችበት ታህሳስ 26/09 ዓ.ም በማራኪ ግቢ ድህረ ምረቃ ህንፃ የቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ቲያትር አዳራሽ ተካሂዷል፡፡

መርሀ ግብሩ ለሁለትቀናት የተካሄደ ሲሆን በሁለት ዋና ዋና ተግባራትም ተከናውኗል፡፡ በትምህርታዊ ጉባኤና በአዝናኝ ጥበባዊ ድግስ፡፡ በትምህርታዊ ጉባኤው የትምህርት ክፍሉ ባልደረባ የሆኑትና በአሁኑ ወቅት የ2ኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ኒቨርሲቲ በመከታተል ላይ የሚገኙት መምህር ቴወድሮስ “the sought aesthetical execution of art through the lenses of philosophers and theorists” የጥበብ አካሄድ በዘርፉ ፈላስፎችና ንድፈሀሳባውያን መነፅር ምን ይመስላል፣ በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፁሁፍ አቅርበዋል፡፡ በጥናታዊ ፁሁፋቸውም ጥበብ ምንድን ናት; አገልግሎቷስ ምን ይመስላል; ጥበብ ለማህበራዊ ፋይዳና ጥበብ ለራሷ ፋይዳ የሚሉ ሁለት ፅንፍ ሀሳቦች ተዳስሰውበታል፡፡

ጥናታዊ ፁሁፋን ተከትሎም በታዳሚ መምህራን፣ ተማሪዎችና ተሳታፊ እንግዶች በቀረቡ ጥያቄዎችና ሀሳቦች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱም የሀገራችን የኪነጥበብ ስራዎችና ውጤቶችን አስመልክቶ አካሄዱ ምን መምሰል አለበት፣ በዘርፉ ጠንካራ የሆነ ተተኪ ትውልድ ለመፍጠር ተማሪዎቹ ላይ ምን መሰራት አለበት፣ ከትምህርት ክፍሉስ ምን ይጠበቃል የሚሉ ሀሳቦችና ተያያዥ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡

በጥበባዊ ድገሱም የሎሬት ፀጋየ ገ/መድህንን ስራዎች የሚዘክር ይዘት ካለው የፕሮፌሰር ፔትሮቶጅያን የግጥም ስራ በተጨማሪ በትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች በርካታ አስናኝ ግጥሞችና መነባንቦች ቀርበዋል፡፡ በተጨማሪም በዝግጅቱ ተጋባዥ የነበረችውና በብሄራዊ ትያትር ተዋናይት፣ አዘጋጅና የትያትር እነፃ ባለሙያ እንዲሁም በበርካታ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ስራዎች የምትታወቀው አርቲስት መሰረት ህይወት የህይመት ተሞክሮዋን ለታዳዉ አጋርታለች፡፡

በመጨረሻም በአርቲስት ፍስሀ በላይ ይማም የተፃፈና በትምህርት ክፍሉ የ3ኛ ዓመት ተማሪዎች የተዘጋጀና የተከወነ አልቃሽና ዘፋኝ የተሰኘ የሙሉ ጊዜ የኮሜዲ ቲያትር ቀርቧ ታዳሚውን አዝናንቷል፡፡

