የታሪክ ተመራማሪና የመብት ተሟጋች የኢትዮዽያ ወዳጅ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንከርስት ህልፈተ ህይወት
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት፣ ህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬትና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በሙሉ ታላቁ የታሪክ ተመራማሪና የመብት ተሟጋች የኢትዮዽያ ወዳጅ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንከርስት ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልፃል፡፡ሪቻርድ ፓንክረስት በእንግሊዝ ሀገር በ1920 ዓ.ም ከተማረ እና ተራማጅ ከሆነ ቤተሰብ ተወለዱ፡፡ እናታቸው ኢስቴል ሲሊቫ ፓንክረስት ስለ ኢትዮዽያ በቂ ዕውቀት የነበራቸው፣ የፋሽስት ስርዓት ተቃዋሚና ለሴቶች መብት የሚከራከሩ ጠንካራ ሴት ነበሩ፡፡

ፕሮፌሰር ፓንከርስት ትምህርታቸውን እንግሊዝ ሀገር ውድፎርድ ከሚገኘው ባንክሮፍት ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡የፒ.ኤች.ዲ ትምህርታቸውን በምጣኔ ሀብት ታሪክ ካገኙ በኃላ ወደ ኢትዮዽያ በመምጣት ከ1949ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በአሁን አጠራሩ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተማር ጀመሩ፡፡በ1955ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘውን የኢትዮዽያ ጥናት ተቋምን አቋቁመዋል፡፡የተቋሙ የመጀመሪያው ዳይሬክተርም ነበሩ፡፡እኒህ ታላቅ ሰው ለኢትዮዽያ ካበረከቷቸው በርካታ ስራዎች አንዱና ዋናው ይህ ነው ማለት ይቻላል፡፡የኢትዮዽያ ታሪክ ምርምርና ትምህርት ማዕከል በመሆን በአለም እንዲቀጥል ያስቻለ ትልቅ ተቋም ነው፡፡
በ1969ዓ.ም በነበረው የስርዓት ለውጥ ፕሮፌሰሩ ኢትዮዽያን ለቀው ወደ ሀገራቸው እንግሊዝ ተመልሰዋል፡፡ለቀጣይ 10 ዓመታትም በሮያል አላስቲክ ሶሳይቲ በላይብራሪያንነት አገልግለዋል፡፡ከ10 ዓመታት በኃላ ወደ ኢትዮዽያ የተመለሱት ፕሮፌሰር ፓንክረስት በኢትዮዽያ ጥናት ተቋም እንደገና የምርምር ስራቸውን ጀመሩ፡፡
ፕሮፌሰር ፓንክረስት 22 የሚሆኑ መፃህፍትን በግላቸውና ከሌሎች አካላት ጋር በጋራ በመሆን ፅፈዋል እንዲሁም 17 መፃህፍትን በመገምገም ስለ ኢትዮዽያ ታሪክ በመፃፍ ለዓለም አስተዋውቀዋል፡፡የኢትዮዽያን ባህልና ወግ የሚገልፁ ከ400 በላይ የሚሆኑ አርቲክሎችን በመፃፍ በተለያዩ መፅሄቶችና ጋዜጣዎች በማሳተም የኢትዮዽያን መልካም ገፅታ ገንብተዋል፡፡ፕሮፌሰር ፓንክረስት የአክሱም ሀውልት ወደ እናት ሀገሩ እንዲመለስና ቀድሞ ወደነበረበት ቦታ ተመልሶ እንዲቆም ያደረጉት ከፍተኛ ጥረትም ሌላው ተጠቃሽ ስራቸው ነው፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ በሙሉ በታላቁ የታሪክ ተመራማሪና የመብት ተሟጋች ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ህልፈተ ህይወት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለፅን፣ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
እና
ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት

