እንቦጭ አረምን ለማስወገድ የሰው ኃይል የማይተካ ሚና እንዳለው ተገለጸ
ጣና ሐይቅ 84 ኪ.ሜ ርዝመትና 66 ኪ.ሜ ስፋት እንዲሁም ከ 15 ሜትር በላይ ጥልቀት እንዳለው ይነገርለታል፡፡ በተለያዩ ደሴቶቸም በርካታ ገዳማትን አቅፎ ይዟል፤ በዙሪያው ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችም በተለያየ መንገድ የገቢ ምንጭ ነው፡፡ ጣናን ተንተርሰው በመዝናኛው ኢንደስትሪ፣ በአሳ ማጥመድ፣ በማስጎብኘት እና በሌሎችም የስራ መስኮች ተሰማርተው ኑሮቸውን የሚገፉ በርካቶች ናቸው፡፡
ጣና የአማራ ክልል ወይም የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም ጣና የምስራቅ አፍሪካ ብሎም የአለም ቅርስ ነው፡፡ ከቅርስነትም አልፎ ህይወት ነው፡፡ ጣና ከሌለ በዙሪያው የሚገኙ በቀጥታ ተጠቃሚ የሆኑ ከ ሶስት ሚሊየን በላይ ዜጎች አደጋ ላይ ይወድቃሉ፡፡
ሆኖም ይህ ብዙ ብዙ የሚባልለት ጣና በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ ከዛሬ አምስት አመት በፊት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በጣና ሐይቅ እንደተከሰተ የሚነገረው እንቦጭ የተባለ አረም በጣና ሐይቅ ህልውና ላይ የተጋረጠ ከፍተኛ አደጋ ሆኗል፡፡
ይህንን አረም ለማስወገድ ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ አረሙ በፍጥነት የሚራባና ዘሩ ለረጅም አመታት በመሬት ውስጥ የሚቆይ በመሆኑ እርጥበት ሲያገኝ እንደገና እየበቀለ የማስወገድ ሂደቱን ፈታኝ አድርጎት ቆይቷል፡፡
በአሁኑ ሰዓትም አረሙ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ በመሄድ ላይ ሲሆን ዘለቄታዊ መፍትሄ ካልተገኘለት ከፍተኛ የሆነ ውሃን የመምጠጥ ኃይል ያለው በመሆኑ በሐይቁ ላይ በጣም አስከፊ የሆነ ጉዳት እንደሚያስከትል ግልፅ ነው፡፡
በአማራ ክልል የሚገኙ ሰባት ዩኒቨርስቲዎችም እንቦጭ አረምን ለመቆጣጠር ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ፎረም ተቋቁመዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲም ይህንን አረም ለማስወገድ ሳይንሳዊ እና መካኒካል የሆኑ ተግባራት ቀደም ብሎ በመጀመር ወደ እንቅስቃሴ ገብቷል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ በማቀድ በየሳምንቱ በዘመቻ መልክ የሚከናወን አረሙን በሰው ኃይል የማስገድ ስራ እየተሰራ እንደሆነና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር በተለይ በጎርጎራ አካባቢ የሚገኘውን የጣናን ክፍል ከአረሙ ነፃ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑን የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ፕ/ር መርሻ ጫኔ ገልፀዋል፡፡
ፕ/ር መርሻ አያይዘውም አረሙን የማስወገድ ዘመቻ ለአራት ሳምንታት ያህል የተካሄደ እንደሆነና በቀጣይም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር ስራው ያለማቋረጥ በየሳምንቱ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል፡፡
ባለፉት የአራት ሳምንታት ዘመቻ፣ የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ የደጋፊ ማህበር አባላት፣ የተለያዩ የወጣት ማህበራት፣ የእድር ማህበራት ፣ መንፈሳዊ ማህበራት፣ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች እና ሌሎችም ተሳትፈዋል፡፡
በአሁ ሰዓት የተለያዩ ማህበራት እና ሌሎችም አካላት አረሙን ለማስወገድ የሚደረገውን ዘመቻ ለመቀላቀል ወረፋ በማስያዝ ላይ መሆናቸው እና የህዝቡ ተሳትፎ እጅግ አስደሳች እንደሆነ የገለፁት ፕ/ር መርሻ በኬሚካል፣ በባዮሎጂካል እና በማሽን የማስወገድ ፣ የውሃ ላይ አጥር በማጠር የመገደብ ስራ እንዲሁም ሌሎች ጉዳት የማያደርሱ እና ለጨፊነት የሚያገለግሉ የአረም ዝርያዎችን የማስፋፋት ስራ ወደፊት እንደሚከናወን ገልፀዋል፡፡
ፕ/ር መርሻ አያይዘውም ዉሃው ዙሪያ ያለውን አረም በማሽን ማስወገድ እንደማይቻል እና ማሽኑ ገፍቶ ወደ ዳር የሚያመጣውንም አረም ከሰው ኃይል ውጭ ማስወገድ እንደማይቻል ገልፀው ለዚህም ምንም ያህል ኬሜካል ሆነ ባዮሎጂካል መንገድ፤ ሌሎችንም ማሽኖች ብንጠቀምም የሰው ኃይል የማይተካ ሚና ስላለው ወደፊት በየሳምንቱ በሚደረጉ አረሙን የማስወገድ ዘመቻዎች አሁን ያለው የህዝብ ተነሳሽነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዘገባ — ደጄ አማረ

