ደረጃቸውን ባልጠበቁ የቤቶች አሰራር እና ህገወጥ ግንባታዎችን ዙሪያ ውይይት ተካሄደ
በጎንደር ዩቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስና ስነሰብ ኮሌጅ አስተባባሪነት ደረጃቸውን ያልጠበቁ የቤቶች አሰራር እና ህገወጥ ግንባታዎችን ለማሻሻል ከመስከረም 19-20/ 2010 ዓ.ም በታየ በላይ ሆቴል መሰብሰቢያ አዳራሽ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን የመክፈቻ ንግግር በተጀመረው በዚህ መድረክ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ከመቀሌ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች የሚመለከታቸው ምሁራን፣ ከኢትዮጵያ የህንፃ ዲዛይን እና ከተማ ልማት ተቋም፣ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ተጋባዥ እንግዶች፣ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስና ስነሰብ ኮሌጅ የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች እንዲሁም አውሮፓ ሀገር ከሚገኙ ሶስት አጋር ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ምሁራን ተገኝተዋል፡፡
[widgetkit id=7033]
የምክክር መድረኩ ያተኮረው የህገወጥ ግንባታንና ደረጃቸውን ያልጠበቁ የቤቶች አሰራርን እንዴት እናሻሽል? በሚል ርዕሰ ጉዳይ በተቀረፀ ፕሮጀክት ዙሪያ ሲሆን፣ ይህ ፕሮጀክት በሦስት ኢትዮጵያዊ ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም በጎንደር፣ በመቀሌና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በሦስት አውሮፓዊ ዩኒቨርሲቲዎች የጋራ ትብብር የሚካሄድ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ Social inclusion and Energy Management for Informal Urban Settlements (SES) የሚል ስያሜ ሲኖረው የገንዘብ ድጋፉ ከአውሮፓ ኮሚሽን መገኘቱን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የስነ ህዝብ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶ/ር አፀደ ደስታ ተናግረዋል፡፡
የዚህ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ዋና አላማ ይህን ፕሮጀክት ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብና በማስተዋወቅ ከውይይቱ የሚነሱ ሀሳቦችንና ጥቆማዎችን በመውሰድ ፕሮጀክቱ ምን ላይ ትኩረት በመስጠት መስራት እንዳለበትና ፕሮጀክቱን ለማጠናከር የሚረዱ ግብአቶችን ለመውሰድ ነው፡፡ ከውይይቱ የሚነሱ ሀሳቦችም በሚመለከታቸው የትምህርት ክፍሎቸ በሚደረጉ የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያዎች ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን መምህርቷ ተናግረዋል፡፡ መምህርቷ አያይዘውም ለዘላቂ የልማት ግብ (Sustainable Development Goals) የሚሰሩ የሰለጠኑ የስነ ህንፃ ባለሙያዎች፣ የከተማ ንድፍ አውጭዎች እና የማህበረሰብ አጥኝዎች ንቁ ተሳትፎ እንደሚጠበቅ አስታውሰዋል፡፡
ከፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዳኑቢ ዩኒቨርሲቲ ክሬም የመጡት ዶ/ር ታኒያ በርገር ስለ ፕሮጀክቱ አላማ የሚያሰረዳ ፅሁፍ ካቀረቡ በኋላ ለአጠቃላይ ውይይቱ መነሻ የሚሆኑ አስር ያህል ጥናታዊ ፅሁፎች በተለያዩ አካላት ቀርበዋል፡፡ በመጨረሻም በጥናታዊ ፅሁፎች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡
ዘጋቢ መሰረት አለምነህ

