የልዑካን ቡድኑ ጎንደር ገባ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ2009 በጀት ዓመት ባሳየው የላቀ አጠቃላይ አፈጻጸም በሀገራችን ከሚገኙ ነባር ዩኒቨርሲቲዎች ለ2ኛ ጊዜ 1ኛ በመሆን እና ከአትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት አሁንም ለ2ኛ ጊዜ የ1ኛ ደረጃ የጥራት ተሸላሚ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ ዓመቱን በስኬት በማጠናቀቅ የድርብ ድል ባለቤት መሆኑ ከተሰማ ጀምሮ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ የተለያዩ አጋር አካላት እንዲሁም የጎንደር ከተማ አስተዳደር፣ የጎንደር ከተማ እና የአካባቢው ማህበረሰብ ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
ልዑካን ቡድኑን በመምራት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ እና የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት ዓጸደወይን ዋንጫዎችን በመያዝ ዛሬ ጥቅምት 16/2010 ዓ.ም ጎንደር አፄ ቴድሮስ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ በመቀጠል በዩኒቨርሲቲው ግቢዎች በመዘዋወር የልዑካን ቡድኑና ሌላው ማህበረሰብ ደስታቸውን በጋራ ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም በፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ህንጻ መናፈሻ በሻይ ቡና ዝግጅት ፕሮግራም ተጠናቋል፡፡
በሻይ ቡና ዝግጅቱ ወቅት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ውጤቱ በጋራ ርብርብ የመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለወደፊትም ዩኒቨርሲቲውን ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ እንዲሁም በዓለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ተቋም እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ፣ ለዩኒቨርሲቲው አጋር አካላት፣ ለጎንደር ከተማ አስተዳደር፣ ለጎንደር ከተማ እና ለአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም እንኳን ደስ አላችሁ እንኳን ደስ አለን!
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

