ታሪካችንና ባህላችን በዘጋቢ ፊልም” በሚል ርዕሰ ጉዳይ አውደ ጥናት ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የፊልምና ቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ትምህርት ክፍል በ2010 የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ዲግሪ በ9 ተማሪዎች ስራ የጀመረ የትምህርት ክፍል ነው፡፡ ትምህርት ክፍሉ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሲሆን፣ በሙያው ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር ለመቅረፍ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ለዚህም የተለያዩ ባለሙያዎችንና በሙያው ልምድ ያላቸውን አርቲስቶች በመጋበዝ ተቋሙ አቅሙን በመገንባት ላይ ነው፡፡
[widgetkit id=7234]
ከዚህም መካከል አንጋፋውን የቲያትርና የፊልም ባለሙያ አርቲስት ደበበ እሸቱን በመጋበዝ “ታሪካችንና ባህላችን በዘጋቢ ፊልም እይታ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ህዳር 1/2010 ዓ.ም በማራኪ ግቢ የቴአትር ጥበባት አዳራሽ አውደ ጥናት አካሂዷል፡፡ በዚህ አውደ ጥናት የማህበራዊና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ካሳሁን ተገኝን ጨምሮ የኮሌጁ መምህራን፣ ተማሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡ ዶ/ር ካሳሁን ተገኝ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን፣ ኮሌጃቸው መምህራንና ተማሪዎች ሊማሩባቸውና ልምድ ሊለዋወጡባቸው የሚችሉ ሰሚናሮችን እንደሚያካሂድ ገልፀው፣ በዚህ ሴሚናር ደግሞ መምህራን በተለይ ደግሞ በኪነ ጥበብ ዘርፍ ተተኪ የሆኑ ተማሪዎች ትልቅ ልምድ እንደሚወስዱ በመክፈቻ ንግግራቸው ተናግረዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ለውይይት መነሻ የሚሆን ፅሁፍ በአርቲስት ደበበ እሸቱ ቀርቦ በመምህራንና በተማሪዎች ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በፅሁፉም ባህልና ታሪክን ለሌሎች ከምናካፍልባቸው መንገዶች አንዱ ዘጋቢ ፊልምን በመጠቀም መሆኑ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ፊልም አንድን ባህል ለማዳንም ሆነ ለማጥፋት ትልቅ መሳሪያ መሆኑን አርቲስት ደበበ ደጋግሞ ተናግሯል፡፡ አርቲስቱ ከመምህራንና ተማሪዎች ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የህይወት ተሞክሮውን ሌሎች ይማሩበታል በማለት አካፍሏል፡፡
ለፊልም ትምህርት ክፍል ተማሪዎች መማሪያ የሚሆኑ እና በአርቲስቱ የተፃፉ ሁለት መፃህፍትን ለዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች በማስረከብ፣ ዩኒቨርሲቲው አሳትሞ ለራሱ ተማሪዎች በነፃ እንዲማሩበትና በሌሎች ክልሎች ለሚገኙ ተማሪዎች በሽያጭም ይሁን በመልካም ፈቃደኝነት በመስጠት እንዲጠቀሙበት ቢያደርግ መልካም ፈቃዳቸው መሆኑን አርቲስት ደበበ ገልጧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አርቲስት ደበበ እሸቱ ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመሆን በእስራኤል ሀገር በቤተ እስራኤላውያን ላይ የተሰራ “ቀያይ ቀንበጦች” (red leaves) የተሰኘ የዘጋቢ ፊልም በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ታይቶ የሚገኘው ገቢ በጣና ውስጥ ያሉ ገዳማት ላይ ዘጋቢ ፊልም እንዲሰራባቸውና ዘጋቢ ፊልሙ ለሽያጭ ወይም ለጨረታ ቀርቦ የሚገኘው ገቢ በጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተውን አስከፊ አረም በዘላቂነት ለመከላከል የሚችል ኃይል ለመፍጠር ይዋል በማለት እነሆ በረከት ብሏል ፡፡አርቲስቱ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ10 ቀን ቆይታው በፊልም ትወና (screen acting) ላይ ያተኮረ ትምህርት ለፊልምና ቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ሰጥቷል፡፡
ይህ አካባቢ በባህልም ሆነ በታሪክ የታደለ እና ለዘጋቢ ፊልሞች መስሪያ ምቹ የሆነ ሁኔታ ቢኖረውም፣ እስካሁን የተሻለ ዘጋቢ ፊልም አለመሰራቱ በሙያው የተማረ የሰው ኃይል ባለመኖሩ መሆኑንና አሁን ግን ትምህርት ክፍሉ መከፈቱ ችግሩን ይቀርፋል ያሉት ደግሞ የፊልምና ቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ምስጋናው አለሙ ናቸው፡፡ አቶ ምስጋናው አያይዘውም በአካባቢው የሚገኙና በሙያው ለመሰልጠን ፍላጎት ላላቸው ግለሰቦች የትምህርት ክፍሉ በተካታይ የትምህርት ፕሮግራም ከሚቀጥለው ሴሚስተር ጀምሮ እንዲማሩ ሁኔታውን እንደሚያመቻቹ ገልፀዋል፡፡
አርቲስት ደበበ እሸቱ በመጨረሻም “ይህንን ዕድል አግኝቸ በሙያየ ተተኪ የሆኑ ተማሪዎችን ለማነጋገር በመቻሌ እጅግ ደስ ብሎኛል ለዚህም ዩኒቨርሲቲውን አመሰግናለሁ” ብሏል፡፡
ዘጋቢ፡ መሰረት አለምነህ
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

