የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፈጠራ ስራ ባለቤቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሽልማት ተበረከተላቸው
የፈጠራና የምርምር ሰዎችን በማበረታታት የሀገሪቱን ቴክኒሎጂ ወደፊት አንድ አርምጃ የሚያራምድ ሀገር አቀፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የሽልማት ስነስርዓት በአዲስ አባባ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ጥቅምት 8 ና 9/2010 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ በዚህ የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባዘጋጀው የሽልማት ፕሮግራም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአራት የወርቅ ሜዳሊያዎች ባለቤት ለመሆን በቅቷል፡፡
በእርግጥም ለተከታታይ አመታት የአጠቃላይ አፈጻጸምና የጥራት የበላይነትን በመጎናጸፍ ታላቅ ክብርን ላገኘው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከዚህ በላይ ይጠበቃል፡፡ይሁንና ይህ ድርብርብ ሽልማት የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ የበልጠ እንዲሰራ የሚያነሳሳ መሆኑን ያሳያል፡፡ በአዳዲስ የፈጠራ ስራዎችና ምጡቅ ሀሳቦች የወርቅ ሜዳሊያ ሽልመት የተበረከተላቸው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና ስታፍ አባላት ዶ/ር ሳሙኤል ሳህሌ፣ አቡሃይ ውብሸት፣እመቤት ክብካብና አዚዛ ኡመር ናቸው፡፡የፈጠራ ባለቤቶቹ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር የተከበሩ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝና ከኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እጅ የሜዳሊያ ሽልማቶቹ ተበርክቶላቸዋል፡፡
የፈጠራ ባቤቶቹን ለሽልማት ያበቋቸው ዝርዝር ስራዎችን በተመለከተ ፣ዶ/ር ሳሙኤል ሳህሌ የድህረ ምረቃ ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ፣ከዳጉሳ ቢራ በመስራት እንዲሁም የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆነው አቡሃይ ውብሸት የላፕቶፕ ባትሪ መሙያ ኬሚካል፣ የሽንት ቤት ሽታ ማስወገጃ ኬሚካልና ሌሎች ፈጠራዎችን በመስራት ሲሆን እነዚህ ፈር ቀዳጂ ስራዎች ሀገራችን ለያዘችው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሽግግር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ይታመናል፡፡
ሌሎች የዩኒቨርሲቲው የፈጠራ ባለቤቶችና የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት ማለትም እመቤት ክብካብ የብረት ዝገት ማስወገጃ/Anti-rust/ ኬሚካል ስትሰራ፣ ሌላኛዋ አዚዛ ኡመር ደግሞ የድጅታል ማስታዎቂያ ሰሌዳ በመስራት ከብዙ የግልና የመንግስት የፈጠራ ተወዳዳሪዎች መካከል ጎልተው ድንቅ የፈጠራ ስራዎቻቸውን አሳይተዋል፡፡
ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በልጦ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአራት ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት መሆን ለሁሉም የዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ ክብር ነው፡፡የመልካም ስራ ሽልማቱ ሌላ ልዩ ስራ ነው እንዲሉ ፣ነገም ከዚህ የተሻለ ሰርቶ ለሀገርና ለአካባቢው ትልቅ ፋይዳ ያለው ስራ ለመስረት ይህ ሽልማት ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ሁሉ ያበረታታል፡፡
በሳሙኤል ማለደ
ትርጉም ፡ ደስታው ዋኘው
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

