1.5 ሚሊየን ብር ዋጋ የሚተመን የተለያዬ የህክምና ቁሳቁስ ለምስራቅ በለሳ ጓህላ ሆስፒታል ድጋፍ ተደረገ፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ መጠነ ሰፊ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ከነዚህም የማህበረሰብ አገልግሎት አበይት ተግባራ መካከል በጎንደር ከተማና አካባቢው ለሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች እያደረገ ያለው የቁሳቁስና የሙያ ድጋፍ ይጠቀሳል፡፡ባሳለፍነው ቅዳሜ ህዳር 16/2010 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲው ከ1.5 ሚሊየን ብር በላይ ሊያመጣ የሚችል የተለያዬ የህክምና ቁሳቁስ ለጓህላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አበርክቷል፡፡
[widgetkit id=7705]
ለአዲሱ ሆስፒታል ከተበረከተለት የህክምና ቁሳቁስ መካከል የህሙማን ተኝቶ መታከሚያ አልጋዎች፣የቀዶ ህክምና መሳሪያዎች፣ ልዩ ልዩ የላቦራቶሪ እቃዎችና የህሙማን መንቀሳቀሻ ወንበሮች/ዊል ቸር/ ይገኙበታል፡፡ በንብረት ርክክብ ወቅት የጓህላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘመነ ሀብቱ እንደገለጹት በአዲሱ ሆስፒታል 40 ያህል የህሙማን የመኝታ ክፍሎች አሉ፡፡ሆኖም ግን በዚህ ሰፊ ሆስፒታል ውስጥ 16 አልጋዎችና በጣም አነስተኛ ሌሎች የህከምና መሳሪያዎች ብቻ የነበሩ ሲሆን አሁን የተደረገላቸው ድጋፍ የህክምና አሰጣጣቸውን በአንጻሩ እንደሚያሻሽለው ተናግረዋል፡፡ስራ አስኪያጁ አያይዘውም ህሙማን ወለል ላይ ተኝተው በመታከማቸው ለህክምና አሰጣጥ ሂደቱ አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ታካሚዎች ለልዩ ልዩ ተላላፊ በሽታዎች እንደሚጋለጡ ገልጸዋል፡፡ በተደረገው የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅና የአካባቢው ነዋሪዎች መደሰታቸውን ገልጸው ለዩኒቨርሲቲው ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በደስታው ዋኘው
የህ/ዓ/አ/ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



