26ኛው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በድምቀት ተከበረ
እንደ አለም አቀፍ የጤና ድርጅት መረጃ ከ1 ቢሊዮን (15%) በላይ የሚሆኑ የዓለማችን ሰዎች ለአካል ጉዳተኝነት የተጋለጡ ናቸው፡፡ ከዚህ አሀዝ በመነሳት የሀገራችንን ስንመለክት 17.6% የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል የአካል ጉዳተኛ እንደሚሆን ይገመታል፤ ከእነዚህም ውስጥ 95% የሚሆነው ህዝብ በድህነት እንደሚኖሩ መረጃዎች ያሳያሉ፤ ይህ ቁጥርም ከእድሜ መግፋት እና በሌሎች ከባድ ህመሞች/chronic diseases ምክንያት እየጨመረ እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
[widgetkit id=7761]
ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካል ጉዳት ጥናት አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ፣ ከጎንደር ከተማ የአካል ጉዳት ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል፣ ከጎንደር ከተማ የአካል ጉዳት ፌዴሬሽን እና ከዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አቀፍ ልማት መልሶ ማቋቋም/CBR ፕሮግራም ጋር በመተባበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ25ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን “ሁሉን አቀፍ ጠንካራና ዘላቂ ማህበረሰብ እንገነባ” በሚል መሪ ቃል ህዳር 24/2010 ዓ.ም በሳይንስ አምባ አዳራሽ በድምቀት አክብሯል፡፡
በበዓሉ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት መርሻ ጫኔ፣ የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ልማት ም/ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መሰረት ካሴ፣ የዩኒቨርሲቲው የአካል ጉዳት ጥናት አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ህይወት አበበ፣ በጎንደር ከተማ የሚገኙ በአካል ጉዳት ዙሪያ የሚሰሩ ጽ/ቤቶችና የተለያዩ ማህበራት ኃላፊዎች፣ የጎንደር ከተማ እና የዩኒቨርሲቲው የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ወ/ሮ ህይወት አበበ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካል ጉዳት ጥናት አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው፣ ዩኒቨርሲቲው ለአካል ጉዳተኞች ልዩ ትኩረት በመስጠት እና ለዩኒቨርሲቲው የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችና ሰራተኞች የተለያዩ ድጋፎች እንዲደረግላቸው በማሰብ እራሱን የቻለ ዳይሬክቶሬት መቋቋሙን ተከትሎ በርካታ ስራዎች በተጠናከረ መልኩ በዳይሬክቶሬቱ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ ለአብነትም ለዩኒቨርሲቲው የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የቁሳቁስ ድጋፎች እንደሚደርግ እና የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች በዳይሬክቶሬቱ ድጋፍ አማካኝነት እንደሚሰጥ ወ/ሮ ህይወት ተናግረዋል፡፡
በጎንደር ከተማና አካባቢው ለሚገኙ የአካል ጉዳተኞች፣ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ፕሮጀክቶች አማካኝነት የቁሳቁስና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን ላለፉት ዓመታት ሲያደርግ መቆየቱን በመክፈቻ ንግግራቸው ያወሱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ተቋማቸው ድጋፉን በማጠናከር በዚህ ዓመት/በ2010 ዓ.ም ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን/ master card foundation/ በተሰኘ ፕሮግራም በአማራ ክልል የሚገኙ ብቃት ኑሯቸው በከፍተኛ ትምህርት የመማር ዕድል ያላገኙ አካል ጉዳት ያለባቸውን 20 ተማሪዎች መልምሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ የገልጹ ሲሆን በቀጣይም በሀገራችን እና በጎረቤት ሀገሮች የሚገኙ አካል ጉዳተኞችን የከፍተኛ ትምህርት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ደሳለኝ በመጨረሻም የማህበረሰቡ ኑሮ ሊሻሻል የሚችለው ማህበረሰቡ ስለአካል ጉዳተኞች ያለው የተዛባ አመለካከት ሙሉ በሙሉ መስተካከል እና አካል ጉዳተኞች የለውጡ አካል እንዲሆኑ በተለያየ መልኩ ማሳተፍ ሲቻል ነው ብለዋል፡፡
በማህበረሰቡ ዘንድ ሰለ አካል ጉዳተኞች ያለው ግንዛቤ ይበልጥ እንዲያድግ ከተፈለገ ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ በዓላትን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ማክበር ፋይዳው የጎላ መሆኑን በመዝጊያ ንግግራቸው የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ ናቸው፡፡ አያይዘውም መሰል ዝግጅቶች በተቀናጀ ሁኔታ መቀጠል እንደሚገባቸው አሳስበዋል ፡፡ ፕ/ር መርሻ በዓሉ በሚያምርና በተሳካ መልኩ እንዲከበር አስተዋጽኦ ላበረከቱና ለተሳተፉ ሁሉ ያላቸውን የከበረ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ድራማ፣ ሙዚቃ፣ መነባንብ እና ግጥሞችን በማቅረብ ለበዓሉ ድምቀት ሆነው የዋሉት የዩኒቨርሲቲው ትያትር እና ፊልም ፕሮዳክሽን ት/ት ክፍል ተማሪዎች ሲሆኑ የተለያዩ ተሰጥኦ ያላቸው የአካል ጉዳተኞችም የሙዚቃና የግጥም ተሰጧቸውን ለተዳሚው አቅርበዋል፡፡
አንዳንድ የአነጋገርናቸው የበዓሉ ታዳሚዎችም በዝግጅቱ መደሰታቸውን ገልጸውልናል፡፡ ለአብነትም ወ/ሮ ጥሩየ አትክልት የጎንደር ከተማ አስተዳደር የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ በዕለቱ ዝግጅት መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የጎንደር ዩኒሲርሲቲ እርሳቸው ከሚመሩት መምሪያና ከሎሎች አጋር አካላት ጋር አለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀንን በቅንጅት ተከብሮ እንዲውል ሁኔታዎችን በማመቻቸቱ ተቋሙን አመስግነዋል፡፡ ወ/ሮ ጥሩየ ለወደፊትም በቀጣይነት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ከዩኒቨርሲቲው ጋር አብረው እንደሚሰሩ ያለቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ዘገባ አምሳሉ ግዛቸው
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



