የፊዚክስ ት/ት ክፍል ኮንፍረንስ አካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ስር የሚገኘው የፊዚክስ ት/ት ክፍል ውጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢታዮጵያዊ የዘርፉ ምሁራን ጋር በጋራ በመተባበር ከታህሳስ 17-18/2009 ዓ.ም የቆየ ኮንፍረንስ በአጼ ቴዎድሮስ ግቢ ድህረ ምረቃ አዳራሽ አካሂዷል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ እና የዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ የተገኙ ሲሆን፣ ሌሎች የሀገር ውስጥና የሀገር ውጪ የዘርፉ ሙያተኞችና ተጋባዥ እንግዶች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የፊዚክስ ተማሪዎች የኮንፍረንሱ ተሳታፊ ነበሩ፡፡
[widgetkit id=7849]
በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ የሚደረጉ ውይይቶች ለዩኒቨርሲቲው ብቻም ሳይሆን ለሀገር እድገት ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን የገለጹት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የሆኑ ሙያዊ ትስስሮች/professional networking/፣ ወጣት ሙህራንን የነጻ ትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግም ባለፈ ባገኙት እውቀትና ክህሎት ሀገራቸውንንና ወገኖቻቸውን በተሻለ መልኩ ለማገልገል እድል እንደሚፈጥር ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ደሳለኝ በመጨረሻም ለዩኒቨርሲቲው የመጻህፍት እና ሌሎች ድጋፎችን ከማድረግ በተጨማሪ ኮንፍረንሱን በማዘጋጀትና በማስተባበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት ለዶ/ር አበበ ከበደ ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ምንም እንኳ በዩኒቨርሲቲው በፊዚክስ ትምህርት ዘርፍ በመማር ላይ ያሉ የሴት ተማሪዎች ቁጥር ከ90% በላይ ቢሆንም፣ በአጠቃላይ በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ የሴቶች ተሳትፎ በሀገር ደረጃ የጎላ አይደለም፡፡ በመሆኑም ኮንፍረንሱ በዘርፉ በመማር ላይ ያሉ የዩኒቨርሲቲው ሴት ተማሪዎችን ለማበረታታት እና ለትምህርቱ ይበልጥ ፋላጎት ኢንዲኖራቸው ለማድረግ ዓላማ ያደረገ መሆኑን የጠቀሱት የፊዚክስ ት/ት ክፍል ሀላፊ የሆኑት አቶ ዮናስ እንዳለ ናቸው፡፡ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር እውቅ የሆኑ ምሁራን ጥናታዊ ጹሁፋቸውን እንዲያቀረቡ ማድረግ፣ በቀረቡት ጹሁፎች ላይ የተደረገው ውይይት በቅርቡ ለሚከፈቱ በፊዚክስ ትምህርት ዘርፍ የፒ ኤች ዲ/Phd/ ፕሮግራሞች ለግብዓትነት መጠቀም እና የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን የውጭ ሀገር ነጻ የትምህርት እድል እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ የተለያዩ ልምዶችን ማካፈል የኮንፍረንሱ ተጨማሪ ዓላማዎች እንደሆኑ የትምህርት ክፍሉ ሀላፊ ተናግረዋል፡፡
የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎችም ስለፊዚክስ ትምህርት በቂ የሆነ ግንዛቤ እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡ ለአብነት ያህል የ3ኛ ዓመት የጅዮ ፊዚክስ ተማሪ የሆነችው ደስታ ስዩም፣ ያአላቸውን ሰፊ ልምድ ለማካፈል ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በመጡ ምሁራን በቀረበው ጽሁፍና በተደረገው ውይይት ስለፊዚክስ ትምህርት ዘርፍ በቂ ግንዛቤ ከማግኘትም ባሻገር ብዙ አስተማሪ የሆኑ የህይወት ልምዶችን እንዳገኘች ተናግራለች፡፡
ዘጋቢ፡ አምሳሉ ግዛቸው

