የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ ነው
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮ ማስመዝገብ የሚኖረውን ፋይዳ በተመለከተ ጥር 08/2010 ዓ.ም በማራኪ ግቢ አልሙኒየም ህንፃ አዳራሽ የፓናል ውይይት ተካሄደ፡፡
በፓናል ውይይቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ፣ የኮሌጁ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተጋበዙ እንግዶችና ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኋን የመጡ ጋዜጠኞች ተገኝተዋል፡፡
[widgetkit id=8119]
የፓናል ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ‹‹ብዙ ቅርሶች በተመዘገቡና አለምአቀፍ እውቅና ባገኙ ቁጥር የቱሪስት ፍሰትን በማሳደግ አካባቢው ከቱሪዝም ሀብት መጠቀም የሚያስችለውን እድል ይፈጥራል›› ብለዋል፡፡ ዶ/ር ደሳለኝ አያይዘውም ተማሪዎችና መምህራን አንድን ቅርስ ለማስመዝገብ ሂደቱ ምን እንደሚመስል ያለውን ዕውቀት ከፓናል ውይይቱ በመቅሰም እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ ለመወያያ የሚሆኑ ሁለት ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበዋል፡፡ የመጀመሪያዋ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅራቢ ከኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ-ፅሁፍ (አማርኛ) ትምህርት ክፍል የመጡት መምህርት አዲሴ ያለው ሲሆኑ፣ በጥምቀት በዓል ታሪካዊ አመጣጥና በዓሉ በተለይ በጎንደር ከተማ ደምቆና ልዩ ሆኖ እንዲከበር ነገስታት ያበረከቱትን አስተዋፅኦ የሚዳስስ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ በመቀጠልም ከቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መምህር እንግዱ ገብረወልድ ጥምቀትና ዩኔስኮ በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሁፋቸውን አቅርበዋል፡፡ በጥናታዊ ፅሁፋቸውም አንድን ቅርስ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚከናወኑ ሂደቶችን ዳስሰው በተለይ በሚዘጋጀው የማስመረጫ ሰነድ ላይ ለሚካተቱ አስፈላጊ ጉዳዮች ትኩረት መሰጠት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጥምቀት በዩኔስኮ ቢመዘገብ የሚኖረውን ባህላዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አብራርተዋል፡፡
የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ ቢመዘገብ፣ ለቅርሱ ጥበቃ የሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ፣ ለሀገሪቱ ህዝቦች ይዞት የሚመጣው ክብርና ኩራት እንዲሁም ከሙያ ድጋፍ አንፃር የሚገኙ ጥቅሞች በቀጥታ የሚታዩ ሲሆን ከዚሁ በተጨማሪ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ለሀገሪቱ የገፅታ ግንባታና ለቱሪዝም እድገት ያለውን አስተዋፅኦ በቃላት የማይገለፅ ነው ብለዋል አቶ እንግዱ በጥናታዊ ፅሁፋቸው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ቅርሱ ከተመዘገበ በኋላ ባለቤት የማጣት ስጋት፣ የተለመደውን ሀይማኖታዊ ክንዋኔ ላይ ሊመጣ የሚችል ተፅዕኖና ከሀገሬው ህዝብ ይልቅ ለውጭ ሀገር ዜጎች ተኩረት የመስጠት ሁኔታዎች ቅርሱ በዩኔስኮ ቢመዘገብ ሊታዩ የሚችሉ ጉዳቶች ይሆናሉ ሲሉ ፅሁፋቸውን አጠቃለዋል፡፡
ጥናታዊ ፅሁፎችን ተከትሎ በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው ተጨማሪ ሀሳቦችና ለተጠየቁ ጥያቄዎችም ምላሾች ተሰጥተው ውይይቱ ተጠናቋል፡፡
ዘጋቢ መሰረት አለምነህ
ህዝብና አለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

