የራስ አገዝ ቡድን ፕሮጀክት /Self Help Project/ የፕሮግራም ማስጀመሪያ ውይይት አካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሚከናወኑ በርካታ ማህበረሰብ አቀፍ የምርምር ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የራስ አገዝ ቡድን ፕሮጀክት የፕሮግራም ማስጀመሪያ የማህበረሰብ ውይይት በጎርጎራ መናፈሻ ጥር 26/2010 ዓ.ም አካሄደ፡፡በውይይቱ የሚመለከታቸው አካላት ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ከጎንደር ዙሪያ ወረዳና ከምዕ/ደንቢያ ወረዳ እንዲሁም ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተገኝተዋል፡፡
በማህበረሰቡ ውስጥ የሴቶችን ታላቅ ሚና ለመግለጽ ብዙ ጊዜ፣ ሴቶችን ማስተማር ህብረተሰብን ማስተማር ነው ፤ ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ ጀርባ አንዲት ስኬታማ ሴት አለች ይባላል፡፡ እንዲያውም ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ ጀርባ ከምንል ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ ጎን አንዲት ስኬታማ ሴት አለች ማለቱ የሴቶችን ሁለንተናዊ እኩል ሚና ያሳያል፡፡ በቂ ነው ማለት ባያስደፍርም በርካታ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሴቶችን አቅም ለማጎልበት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም አንዱ የራስ አገዝ ቡድን ፕሮጀክት / Self Help Project / ነው፡፡ የራስ አገዝ ቡድን ፕሮጀክት የሴቶችን ሁለንተናዊ አቅም ለማጎልበት አልሞ ለመስራት የተነሳሳ የማህበረሰብ አገልግሎት ነው፡፡ የህብረተሰቡ ግማሽ ክፍል የሆኑትን ሴቶች አቅም ማጎልበት የአካባቢን ብሎም የሀገርን እድገት ሙሉ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፈንታው ለስራው መሳካት ዩኒቨርሲቲው ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
[widgetkit id=8237]
የራስ አገዝ ቡድን ፕሮጀክት ዋና አስተባባሪና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ኮሌጅ የግብርና ኤክስቴንሽን መምህር የሆኑት፣ አቶ ከፋለ እንየው የፕሮጀክቱን አላማ አስመልከተው ሲገልፁ፣ በገጠር አካባቢ የሚገኙ ሴቶቸን በራስ አገዝ ቡድን በማደራጀት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በአመራር አቅማቸውን ማብቃት ነው ብለዋል፡፡በተለይ በአንጻራዊ ዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚገኙና የተገለሉ የሚመስሉ ሴቶች ላይ በማተኮር ተደራጅተው የተሻለ የገቢ ምንጭ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ በማህበረሰቡ ውስጥ እንደማንኛውም ሰው ጥሩ ግንኙነትና መሰረታዊ የማንበብና የመጻፍ አድል እንዲኖራቸው ማገዝና ማህበራቸውን ወይም ቡድናቸውን በመምራት የአመራር ብቃታቸውን ማሳደግ የፕሮጀክቱ ዋና ዋና ትኩረቶች መሆናቸውንም አስተባባሪው ገልፀዋል፡፡
የፕሮጀክቱን አሰራር በተመለከተም ከ15-20 የሚሆኑ በኑሮም ሆነ በእድሜ ደረጃ ተመሳሰሳይ የሆኑ ሴቶች በአንድ ቡድን የሚደራጁ ሲሆን በተስማሙበት ልክ አነስተኛ የሆነ ሳምንታዊ ቁጠባ ያደርጋሉ፡፡ የብድር ስርአትም ይኖረዋል፤ ቀስ እያለም ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ትስስር ይፈጥራሉ፡፡ የራስ አገዝ ቡድን ከሌሎች የህብረት ስራ ማህበራትም ሆነ ዩኒየን ልዩ የሚያደርገው የራሱ ባህሪያት አሉት፡፡ በራስ አገዝ ቡድን የሚደራጁ አባላት ፈርጀ ብዙ አቅማቸውን ማለትም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ብቃታቸውን ነው ሚያጎለብቱት፡፡ የሚደራጁትም በአካባቢና በኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ተመሳሳይ የሆኑ ሴቶች ናቸው፤ቡድኑን የሚመሩት የቡድኑ አባለት ብቻ ሲሆኑ ይኸውም በዙር /Rotational/ ይሆናል በማለት አቶ ከፋለ ያብራራሉ ፡፡
አያይዘውም ፕሮጀክቱን ለማስጀመር ሁለት ቀበሌዎች ማለትም ከጎንደር ዙሪያ ወረዳ ታች ፀዳ ቀበሌና ከምዕ/ደንቢያ ወረዳ ደግሞ ጎርጎራ ቀበሌ ተመርጠው እንቅስቃሴ እየተጀመረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሁለቱ ቀበሌዎቹ የተመረጡበትን ዋነኛ ምክንያት ሲገልፁም ታች ጸዳ ለዩኒቨርሲቲው ቅርብ ከመሆኑ የተነሳ ለክትትል ምቹ ይሆናል ብሎ ከማሰብ ሲሆን ከዚህ በፊት በተሰራው የዳሰሳ ጥናት መሰረት ጎርጎራ አከባቢ የሚገኙ ሴቶች በአንጻሩም ቢሆን ከሌሎች አካበቢዎች ትንሽ ዝቀተኛ በሆነ የኑሮ ደረጃ ያሉ መሆናቸው በመረጋገጡ ነው ብለዋል፡፡
በደስታው ዋኘው
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

