ለውጤታማነት በጋራ መሥራት
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሰሜን ጎንደር ዞን ከሚገኙት የተለያዩ ወረዳዎች የምርጥ ዘር ምርምር በማካሄድ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡ከእነዚህም ውስጥ ቋራ፣ምዕራብ በለሳ፣ ዳባት ወረዳዎች ይገኙበታል፡፡
የዳባት ምርምር ማዕከል በ2005 ዓ.ም ሥራውን የጀመረ ሲሆን ከ13 በላይ ዓይነት ያላቸው የድንች ዘሮችን በማሰባሰብና በምርምር በማረጋገጥ ለአርሦ አደሮች ማሰራጨት ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ምርምር መዕከሉ በአለፉት ዓመታት ያገኛቸውን መልካም ውጤቶች መነሻ በማድረግ በቀጣይ የድንች ዘር ስርጭት መጠኑን አሁን ካለበት 100 ኩንታል ወደ 5 እጥፍ ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል፡፡ሥራውን ወጤታማና ተደራሽ ለማድረግ፣ የምርምር ማዕከሉ ከሚገኝበት ከዳባት ወረዳ ጋር በትብብር ለመስራት ስምምነቱ አስፈላጊ በመሆኑ መጋቢት 1/2010 ዓ.ም በዳባት ወረዳ የገብርና ገጠር ልማት ጽ/ቤት እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስምምነት ውል ተፈራርመዋል፡፡
[widgetkit id=8359]
በፊርማ ስነሥርዓቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፈንታው እና የዳባት ወረዳ ግብርናና ገጠር ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ እንዳልክ አማረ የተገኙ ሲሆን ስምምነቱን አስመልክቶ አጭር ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ በምርምር የተደገፈ የድንች ዘሮችን ማቅረብ ፣የማዳበሪያና የውሃ ምጣኔን በምርምር አስደግፎ ማቅረብና አጫጭር ስልጠናዎችን መስጠት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በኩል የሚከናወን ሲሆን የድንች ዘሩን በተመረጡ ቦታዎች ላይ ከማሰራጨት ጀምሮ እስከ ምርት ድረስ ድጋፍና ክትትል ማድረግ፣ አርሦ አደሮቹ የሚወስዱትን ዘር ነፃ እነዳልሆነና በወሰዱት ልክ ዘሩን መመለስ እንዳለባቸው ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ የወረዳው ግብርናና ገጠር ለማት ጽ/ቤት እመሆን እንዳለበት በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡
የምርምርና ህብረተሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ ምርምር ማዕከሉ የሚጎለብተው በትብብር ሲሰራ መሆኑን ገልጸው የዳባት ወረዳ ግብርናና ገጠር ልማት ጽ/ቤት የድርሻውን ወስዶ ማገዝ እንዳለበትና በቀጣይም ለዘር የተመረጡት ቦታዎችን ጉብኝት በማድረግ ድጋፉ እንደሚቀጥል አሳስበዋል፡፡የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፈንታው በበኩላቸው ዘሩን እዲወስዱ የተመረጡት አርሦ አደሮች ትርፋማ ሆነው የወሰዱትን ዘር መመለስ እንዳለባቸውና የተመለሰው ዘርም በቀጣይ ለሌሎች አርሦ አደሮች የሚሸጋገር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡የዳባት ወረዳ ግብርናና ገጠር ልማት ጽ/ቤት ኃላፊም አቶ እንዳልክ አማረ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለማህበረሰቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ እጅግ አበረታች መሆኑን አድንቀው የድንች ዘር ሥርጭቱ ውጤት አምጭ በሆነ መልኩ በማሰራጨት ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- በላይ መሥፍን
ሕ/ዓ/አ/ግ/ዳይሬክቶሬት

