በአይን ሞራ ግርዶሽና በትራኮማ ህመም የቀዶ ጥገና አገልግሎት እና የዕይታ ችግር ላለባቸው የመነፅር ዕደላ ተደረገ
በቅርቡ በአለም ጤና ድርጅት የተሰራ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በአለም 38 ሚሊየን ያህል አይነ ስውራን ይገኛሉ፡፡ በከፊል ሰሃራማ የአፍሪካ አገራትን ስንመለከት ደግሞ ይህ አሀዝ 7 ሚሊየን ገደማ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በአፍሪካም ሆነ በሌሎች አህጉራት በከፍተኛ ደረጃ የሰዎችን የአይን ብርሃን በመንጠቅ ለአይነ-ስውርነት በማጋለጥ የሚታወቀው የአይን ሞራ ግርዶሽ / ካታራክት/ መሆኑን ጥናቱ አክሎ ያሳያል፡፡ በአገራችንም ይህ ችግር የብዙዎቹ ችግር እንደሆነ የመሰኩ ምሁራን ይናገራሉ፡፡
ይህንን ችግር በመቅረፍ ረገድ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የዐይን ህክምና ትምህርት ክፍል ባለሙያዎች በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በሰሞኑም በቅርቡ ስራ በጀመረው በምስራቅ በለሳ ወረዳ የጉሃላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ላይ ከየካቲት 12/2010 – የካቲት 16/2010 ዓ.ም ድረስ በተካሄደ ዘመቻ በአይን ሞራ ግርዶሽና በትራኮማ ህመም ምክንያት ይሰቃዩ ለነበሩ ህሙማን የቀዶ ጥገና ህክምናና የዕይታ ችግር ለነበረባቸው ሰዎች በምርመራ የመነፅር ዕደላ አካሄደዋል፡፡
[widgetkit id=8413]
የምስራቅ በለሳ ወረዳ፤ ከዞኑ ከተማ ከጎንደር በርቀት የሚገኝ ነው፡፡ስለሆነም ሌላ የተሟላ የህክምና መስጫ ሆስፒታል ባለመኖሩ፤ ከዚህም በተጨማሪ ቦታው ቆላማና ውሃ አጠር በመሆኑ እንዲሁም አቧራማ ስለሆነ በንጽህና ጉድለት ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ለአይን ህመም ህብረተሰቡ ተጋላጭ እንደነበር የጉሃላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡
በዚህም ምክንያት በርካታ ሰዎች ወጣቶችና አረጋውያንን ጨምሮ የሁለቱም አይኖቻቸውን ብርሃን አጥተው ቤት የዋሉ፣ ከትምህርት ገበታ የተለዩ፣ ከምርት ተግባሮቻቸው የተቋረጡ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ የበዛ እንደሆነ በዘመቻ ህክምናው ሲሰጥ እቦታው ተገኝተን አረጋግጠናል፤ ታድያ በመሪ የመጡ ሰዎች ቀዶ ጥገና ህክምና ተደርጎላቸው ብርሃናቸው ተመልሶ ከልብ ሲደሰቱ ከማየት በላይ እርካታ የሚሰጥ ነገር እንደሌለ፤ በተግባር ህሙማንን ሲያክሙ ያገኘናቸው ዶ/ር አሳመረ ፀጋው ገልፀውልናል፡፡ ሁለት አይናቸው አልያም አንድ አይናቸውን ብርሃን ያጡ ከ200 በላይ ህሙማን በዚህ ዘመቻ የቀዶ ጥገና አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ለ225 ሰዎች የዐይን ፀጉር ቀዶ ጥገና፤ ለ163 የዕይታ ችግር ያለባቸው ሰዎችም እንደየችግሮቻቸው በነፃ መነፅር ተሰጥቷቸዋል፡፡በመነፅር መስጠት ተግባር ላይ በስራ ተሰማርታ ያገኘናት ኦፕቲካል ቴክኒሻን የሆነችው ወ/ት ቅድስት ደገፋው መነፅሮቹ ገበያ ላይ ውድ በመሆኑ ከህብረተሰቡ አቅም አንፃር ገዝቶ ለመጠቀም አዳጋች እንደሆነ ከምንም በላይ አገልግሎቱን ለማግኘት ርቀት መጓዝን የሚጠይቅ በመሆኑ፤ ተማሪዎች፣ አርሶ አደሮችና አዛውንቶች በተደረገላቸው ድጋፍ በእጅጉ መደሰታቸውን ገልፃልናለች፡፡ እኛም ቀዶ ህክምና የተደረገላቸውንና መነፅር የተሰጣቸውን አንዳንዶችን አነጋግረናል፡፡
አባ መልካሙ እሸቴ ይባላሉ የምስራቅ በለሳ ነዋሪ ሲሆኑ “ሁለቱም አይኖቼ አያዩም ነበር፡፡ በመሪ ነው ስለህክምናው ከጎንደር ሃኪሞች ይመጣሉ ሲባል ሰምቼ የመጣሁት፡፡ ፈጣሪ እነዚህን ሁሉ” በዘመቻው የተሳተፉ ሀኪሞችን ማለታቸው ነው “እኒህን ላከልኝ አይኔ በራ፤ ይሄ፤ ይላሉ ትኩር ብለው እያዩን የደስታ ሲቃ በቀላቀለ አንደበት “ይሄ የፈጣሪ ስራ ነው “ ብለው ምርቃት በምርቃት ሆኑ፡፡ ለህክምና የተሰባሰበው ህብረተሰብም በእልልታ ደስታውን ሲገልፅ ተመልክተናል፡፡ ብዙዎቹ የእሳቸውን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ አንድ አባት ደግሞ ልጃቸውን ይዘው መጥተው አገኘን፡፡ እኛ ሳንሆን እርሳቸው ሊያነጋግሩን ወደ እኛ መጡ “ይሄ ልጅ የኔ ልጅ ነው ጓደኞቹ ትምህርት ቤት ሲሄዱ፣ ሲጫወቱ ብርሃኑን አጥቶ ቤት በመዋሉ ብዙ ጊዜ በእንባ ስታጠብ አሳልፌአለሁ – አሁን ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምና ባለሙያዎች የዓይን ህክምና ሊሰጡ እንደሚመጡ በቀበሌያችን ሲቀሰቀስ ይዤው መጣሁ፤ ይድናል ብየ እምነት አልነበረኝም፤ እንዲያው ለመሞከር ብየ ነበር የመጣሁት እዩልኝ” አሉ ልጃቸውን ክንዱን ከፍ አድርገው ይዘው አይን አይኑን እየተመለከቱ፤ እሱም ያያቸዋል፤ ማየት ችሏላ “እዩልኝ አሁን ያያል እንግዲህ እንደ ጓደኞቹ ይማራል፣ ይጫወታል፤ መነፅርም እንደሚሰጠው ነግረውኛል፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ምንም አይነት ክፍያ አልከፈልኩም፡፡ ሁሉም አልከፈለም፤ ፈጣሪ ዋጋቸውን ይከፈላቸው፤ አሉ አይናቸውን ወደ ሰማይ አንጋጠው፡፡
ይህ መሰሉ ከልብ የመነጨ ደስታ ለዘመናት ብርሃኑን አጥቶ ከቆየና ብርሃኑ ጋር መልሶ ከተገናኘ ሰው ከዚህም ከዚያም መስማት ለሀኪሞችም በስፍራው ለክትትልና ድጋፍ ለተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል በም/ፕሬዚዳንት ማዕረግ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ሲሳይ ይፍሩ፤ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ቺፍ ክሊኒካል ዳይሬክተርና የዓይን ሀኪም ዶ/ር ፍስሃ አድማሱ፤ የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ስማልኝ አበው እንዲሁም በስፍራው ለተገኘነው የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ከፍተኛ ደስታ የሰጠን ሁኔታ ነበር፡፡
የጉሃላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ዘመነ ሀብቱና የምስራቅ በለሳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጀምበር አያልነህ ከዚህ ቀደም ለሆስፒታሉ ስራ መጀመር ከ1.5 ሚሊየን በላይ የሚያወጡ የህክምና መሳሪያዎች ከዩኒቨርሲቲው መሰጠቱን አውስተው በሆስፒታሉ ለህሙማኑ ለተደረገው ህክምና የዘመቻውን ተሳታፊ ሃኪሞች፤ ጎንደር ዩኒቨርሲቲንና የዩኒቨርሲቲውን ሪፈራል ሆስፒታል አመስግነዋል፡፡ አያይዘውም የዓይን ህሙማን ቁጥር በወረዳው በእጅጉ የበዛ እንደመሀኑ ዘመቻው ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል፡፡ የወረዳው አስተዳዳሪ ከጤናው ዘርፍ በተጨማሪ በትምህርት፣ በግብርና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በርካታ የምርምርና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚጠብቁ ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ዘመቻው የተሳካ ስለመሆኑና ባዩት ሁሉ መደሰታቸውን ገልፀው፤ ለዘመቻው መሳካት የዘመቻውን ቡድን አባላት አመስግነዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኦርቢስ ኢንተርናሽናል፤ ላይት ፎር ዘወርልድ፤ የካርተር ማዕከል፤ ሰሊል ዲ አፍሪካ እና የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ለዚህ መሰሉ ዘመቻ መሳካትና ለሌሎችም እያደረጉ ላሉት ድጋፍ በዩኒቨርሲቲው ስም አመስግነዋል፡፡
ዶ/ር ደሳለኝ በጎሃላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አስተዳዳሪና በምስራቅ በለሳ ዋና አስተዳዳሪ የተነሳውን ጥያቄ አስመልክተው ከዚህ በፊት ለሆስፒታሉ 1.5 ሚሊየን ብር የህክምና ቁሳቁስ መደገፋችንም ሆነ ይህ ዘመቻ ዩኒቨርሲቲያችንና የዩኒቨርሲቲያችን ሪፈራል ሆስፒታል በዞናችንና በአጎራባች ዞኖች አዳዲስ ሆስፒታሎችን የማጠናከርና የመደገፍ ስራዎቻችን አካል ናቸው፤ ይህ ድጋፍም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ብለው የዘመቻውም ጉዳይ ቀጣይ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ከጤናው ዘርፍ በተጨማሪ በሌሎች ዘርፎች የሚኖረውን ድጋፍ በተመለከተ ከዘርፉ ባሙያዎች ጋር በዕለቱ ዉይይት ተካሂዷል፡፡ የዓይን ህክምና ድጋፉን በእብናት ወረዳ ለማካሄድም ከወረዳው ጤና ጥበቃ ጽ/ቤትና አዲስ በመሰራት ላይ ከሚገኘው ሆስፒታል የስራ ኃላፊዎች ጋር አጭር ቆይታ ተደርጓል፡፡ የዐይን ፀጉር ቀዶ ህክምናው ከካርተር ማዕከል በመጣ ባለሙያ ከዘመቻው መጠናቀቅ በኋላም እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ ዘገባ በዩኒቨርሲቲያችን የዕውቀት አድማስ የሬዲዮ ፕሮግራምና፣ የማዕደ አዕምሮ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለአድማጭ ተመልካቾች ተደራሽ ይደረጋል፡፡
ደምሴ ደስታ
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

