አርዓያነት
ኢትዮጵያዊ ናቸው:: ተወልደው ያደጉት ጎንደር ከተማ ነው:: ከ30 ዓመት በላይ ኑሯቸውን አሜሪካን ሀገር አድርገዋል በመሆኑም የአሜሪካዊ ዜግነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በመካኒካል ምህንድስና/mechanical engineering እና በአይ.ቲ/IT ዘርፍ ያገኙ ግለሰብ ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰዓትም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በተመሳሳይ ዘርፍ እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ ለ22 ዓመት በአይ.ቲ ዘርፍ በአሜሪካን ሀገር ሰርተዋል፤ አሁን በግዙፉ የማይክሮ ሶፍት ካምፓኒ/Microsoft Company ውስጥ በአንድ የስራ ዘርፍ ዳይሬክተር ናቸው፣ ኢትዮጵያዊው አቶ መኮንን ካሳ፡፡
አቶ መኮንን ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርማቲክስ ፋካሊቲ ጋር በመተባበር፣ ለፋካሊቲው ተማሪዎችና መምህራን በአይ.ቲ እና ተያያዥ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች የካቲት 21/2010 ዓ.ም በአፄ ቴወድሮስ ግቢ ድህረ ምረቃ አዳራሽ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡
[widgetkit id=8475]
አሰልጣኙም፣ “ዋናው ያነሳሳኝ ነገር፣ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ በርካታ የትምህርት ተቋማት ተከፍተው በተለያዩ ዘርፎች ብዙ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ ታዲያ የኔ ፍላጎት እነዚህ ተማሪዎች በአይ ቲ ዘርፍ በአለም አቀፍ ደረጃ ይበልጥ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከባህር ማዶ ያአገኘሁትን ሰፊ ልምድና እውቀት፣ በራሴ ተነሳሽነት፣ ያለምንም ክፍያ ለማካፈል ነው፡፡” ብለዋል አቶ መኮንን፡፡
አቶ ቴዎድሮስ አለሙ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርማቲክስ ፋካሊቲ ዲን እንደተናገሩት፣ “ስልጠናውን የሰጡት አቶ መኮንን በኮምፒውተር ሙያ ሰፊ እውቀት፣ ክህሎትና ልምድ ያላቸው ግለሰብ ናቸው፡፡ በመሆኑም ለፋካሊቲው ማህበረሰብ፣ ከሱዳን ለመጡ የዩኒቨርሲቲው ሳይንስና ቴክኖሎጂ የፒ ኤች ዲ/Phd ተማሪዎች እንዲሁም ለሚመለከታቸው የዩኒቨርሲቲው ሙህራን ግለሰቡ በውጭ ሀገር የአገኙትን ልምድና ዕውቀት ከማካፈልም በተጨማሪ ከአይ.ሲ.ቲ ጋር ተያያዥነት ያላቸው በርካታ አጋዥ መጻህፍትን ለዩኒቨርሲቲው በስጦታ መልክ አበርክተዋል፡፡” ብለዋል፡፡ በመሆኑም አቶ ቴዎድሮስ አቶ መኮንን ለአደረጉት ድጋፍ በፋካሊቲው ስም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የአነጋገርናቸው አንደአንድ ተሳታፊዎች ከስልጠናው በርካታ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን እንዳገኙ ገልጸውልናል፡፡ ለአብነትም አቶ ወርቁ አበበ በፋካሊቲው የኢንፎርሜሽን ሲስተምስ ት/ት ክፍል ኃላፊ ስልጠናው በሚማርክ አቀራረብ ከመቅረቡም ባሻገር ከአይ.ቲ ጋር የተያያዙ ብዙ ልምድና ዕውቀት እንዳገኙበት ገልጸዋል፡፡ አቶ ወርቁ አያይዘውም መሰል ስልጠናዎች መሰጠታቸው በአለም ዙሪያ ከፍተኛ እድገት እያሳየ የሚገኘውን የአይ.ቲ ዘርፍ ይበልጥ በማወቅና በመተግበር፣ ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ያስችላታል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አምሳሉ ግዛቸው
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

