ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 5ኛውን የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስ አካሄደ
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሀገራዊ የትምህርት ጥራት ጉባኤን ለመጀመሪያ ጊዜ ተነሳሽቱን በመውሰድና በተከታታይ ጊዜያት በማዘጋጀት በሀገር አቀፍ ደረጃ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በየተራ እንዲያዘጋጁ ሀሳብ በማቅረብ ተቀባይነትን እንዲያገኝ አድርጓል፡፡ ለተከታታይ ሁለት አመታት ከነባር ዩኒቨርሲቲዎች የጥራት ከፍታውን የያዘው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ የጥራት ጉባኤው በተከታታይነት እንዲቀጥል ማድረግ ሰፊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው በማሰብ በዚህ ዓመትም የትምህርት ጥራት ኮንፈረንሱን ለ5ኛ ጊዜ አካሂዷል፡፡ “የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ስርዓት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነባራዊ ሁኔታው፣ተግዳሮቶቹና የወደፊት አቅጣጫው” በሚል መሪ ሀሳብ ጉባኤው መጋቢት 7ና 8/2010 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ሳይንስ አምባ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
በጉባኤው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፤ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡
[widgetkit id=8656]
ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፣ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ ለተለያዩ ሀገራት እድገት ምክንያት መነሻ ሆኖ የሚነገርላቸውን ጉዳይ አንስተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹትም በተፈጥሮ ሀብት የበለጸጉ ሀገራት ለእድገታቸው ምክንያት የሆነው ነዳጅ ወይም ወርቅ ሊሆን ይችላል፤ዝቅተኛ የተፈጥሮ ሀብት ለአላቸው ሀገራት ደግሞ አዋጭ ሊሆን የሚችለው በእውቀት የተካኑ መምህራን ፤በልጆቻቸው ትምህርት ላይ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ወላጆችና ታታሪ ተማሪዎችን መፍጠር ነው፡፡ “እውቀትና ክህሎት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጭ ናቸው፣” ያሉት ፕሬዚዳንቱ የሀገራችን ዕድገት እጣ ፈንታ ሊሆን የሚችለውም ጥራት ያለው የትምህርት አሰጣጥን መተግበር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ለትምህርት ጥራት የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት በዚህ ታላቅ ጉባዔ የተለያዩ ጥናቶች መቅረባቸውና ውይይት መደረጉ በትምህርት ጥራት ላይ እየተሰራ ለሚገኘው ስራ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካ/ም/ ፕሬዚዳንት፣ ዶ/ር አስራት አፀደወይን ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው በተከታታይ በየአመቱ የጥራት ኮንፈረንስ ሲያካሂድ ይህ አምስተኛው መሆኑንና ይህም በኢትዮጵያ አንጋፋ ከሚባሉ ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርት ጥራት ተቋሙ የተሻለ እነዲሆን እንዳገዘው ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር አስራት እንደሚሉትም ፣እንዲህ አይነት ጉባኤዎች ሲዘጋጁ ለትምህርት ጥራት አጋዥ የሆኑ ግብአቶች እንዲሟሉ ያግዛል፤ አዳዲስ የአሰራርና የማስተማር ፍልስፍና ልምድ ስለሚቀርብ የመምህራንን አቅም ያጎለብታል፡፡ ስለሆነም ዩኒቨርሲቲው ይህን ጉባኤ ተነሳሽነቱን ወስዶ ከጀመረ በኋላ በትምህርት ጥራት ላይ ለውጥ እያመጣ ይገኛል ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በተከታታይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የጥራት ተሸላሚ መሆኑም ለዚህ ማረጋገጫ ነው፡፡
ለሁለት ቀናት በቆየው በዚህ አገር አቀፍ ጉባዔ ስለትምህርት ጥራት ነባራዊና ፈታኝ ሁኔታዎች፣የተከታታይ ምዘና አሰጣጥና ደሊቨሮሎጂን(ስኬታማነት) የሚመለከቱ ሀሳቦች በተለያዩ ምሁራን ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ጥራት ያለው ትምህርት ስንል፣ “አንድ ተማሪ ትምህርቱን አጠናቅቆ ወደ ስራ ሲሰማራ ለስራ ብቁ ሊያደርገው የሚችል እውቀት፣ ክህሎትና ስነ-ምግባር ያካተተ ትምህርት ነው፣” በማለት የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋየ ሙኸየ አብራርተዋል፡፡ አያይዘውም በትምህርት ጥራት ዙሪያ እየተሰራ ስላለው ስራ ሲገልጹ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ከምስረታ እስከ አተገባበር ያለው አጠቃላይ ሂደት በኤጀንሲው በቅርበት የሚመራ ሲሆን፣ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በተመለከተ ደግሞ ከአደረጃጀቱ ጀምሮ እስከ ፈተና አሰጣጥ ሂደት ያለውን ስታንዳርድ በመከታተል የግምገማና የማሻሻያ ሀሳብ እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል፡፡
የጎልማሳነት ህይወታቸውን በተለያዩ የውጭ ሀገራት ያሳለፉት ተመራማሪ ፕ/ር ማሞ ሙጨ “የኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና በስርዓተ-ትምህርት ውስጥ” በሚለው ቁልፍ ንግግራቸው በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ውስጥ ሀገር በቀል ወግና ስርዓት የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ የራሱን ሳያውቅና ሳያከብር የውጭ ሀገር ባህል አድናቂና ተከታይ እየሆነ ይታያል፤ስለሆነም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደ ግዕዝ ትምህርትና ሌሎች መሰል ሀገር በቀል ሀብትና እውቀትን መሰረት ያደረጉ የትምህርት ፕሮግራሞች ሊከፍቱ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ እንደሚሉትም ሌሎች ሀገራትን ለምሳሌ እንደ ቻይናና ጃፓን ያሉትን ብንመለከት፣ ከሌላው በተጨማሪ የራሳቸውን ቋንቋና ባህል በሚገባ ይማራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ሁሉም ነገር ያደላት ሀገር ሆና ምንም እንደሌላት ልትታይ አይገባም፤ በሀገራችን ትምህርት ውስጥ ለዚህ ለሀገር በቀል ወግ፣ ባህልና እሴት የሚሰጠው ትኩረት ከፍ ሊል ይገባል፡፡እንዲህ ሲሆን ነው ሀገራችን የተሰጣት ጸጋ ሳይበረዝና ሳይደበዝዝ ተጠብቆ መኖር የሚችለው፡፡
ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ፕ/ር ዝናቡ ገ/ማሪያም በበኩላቸው “በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ለትምህርት ጥራት ዋነኛ እንከን ፈጣሪ ከሚባሉት አንዱ የማስተማሪያ ቋንቋው ነው ምክንያቱም እውቀትና ክህሎት በመምህሩና በተማሪው መካከል የሚተላለፍበት መንገድ ቋንቋ ነውና፣” ይላሉ፡፡ መፍትሄውን በተመለከተም ፕ/ር ዝናቡ “እንግሊዝኛ ቋንቋውን አጥብቆ መያዝ ካልሆነም መተው ነው ፣ነገር ግን መተው የሚለው አዋጭነት የለውም፣” ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ስለሆነም መምህራን ፣ተማሪዎችና ፖሊሲ አውጭዎች በትብብር የማስተማሪያ ቋንቋው ላይ ብዙ መስራት እንዳለባቸው አክለው አሳስበዋል፡፡
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የጎልማሶች ትምህርትና ማህበረሰብ ልማት ትምህርት ክፍል ረዳት ፐሮፌሰር ጥሩወርቅ ዘላለም በጉባዔው ሌላኛዋ ተሳታፊና ጥናት አቅራቢ ነበሩ፡፡ “የተከታታይ ምዘና በከፍተኛ ትምህርት አተገባበሩና ተግዳሮቶቹ” በሚል የምርምር ስራቸውን አቅርበዋል፡፡ እንደ ፕሮፌሰሯ ገለጻ፣ ተከታታይ ምዘና ብዙ ሰዎች እንደሚያስቡት በርካታ ፈታናዎችን መስጠት አይደለም ፤ የሰው ልጅ አእምሮም ሆነ አካላት የሚሰሯቸው ስራዎች ጥልቅና ውስብስብ ናቸው፡፡ስለሆነም ይላሉ ፕሮፌሰር ጥሩወርቅ፣ እነዚህን ውስብስብና ጥልቅ ግንዛቤዎች የምንለካባቸው መንገዶችም እንዲሁ ብዙ ናቸው፤ ከተማሪዎቻችን ሁኔታ አንጻር ምዘናዎቻችንን መቃኝት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘውም በትምህርት ጥራት ላይ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተነሳሽቱን በመውሰድ መሰል መድረኮችን ማዘጋጀቱ በተለያዩ ምሁራን የተሰሩ የምርምር ውጤቶች የሚቀርቡበትን አጋጣሚ ከመፍጠሩም ባሻገር ትኩረት የሚሹ ዋና ዋና ጉዳዮችም በተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲያገኙ እንደሚረዳ አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡
ከሰፊው ጉባዔ በመቀጠልም የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የሚመለከታቸው አካላት በየትምህርት ክፍላቸው በተለያዩ ምድቦች በመሆን በውስጥ የትምህርት ጥራት ኦዲትና ስለአጠቃላይ ፈተና ትንተና የቡድን ውይይት ተካሂዷል፡፡
በመጨረሻም በትምህርት ጥራት ጉዳይ ሁሉም የሚመለከተው አካል ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባው የወደፊት አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡
አለምን መቀየር የምንችልበት ዋነኛው መሳሪያ ትምህርት ነው ( Education is the most powerful weapon which you can use to change the world) እንዳለ ታላቁ የጥቁሮች የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ፣ ትምህርት ለአንዲት ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ሚና አለው፡፡ ይሁንና የትምህርት አሰጣጥ ጥራቱ የትምህርትን ሚና ይወስነዋል፡፡የትምህርት ጥራት ስንል የሰው ሀይልና የማቴሪያል ግብአት፣ ምቹ የመማር ማስተማር አካባቢ መኖርና የመሳሰሉት ቅድመ ሁኔታዎች መስተጋብር የሚገኝ ውጤት ነው፡፡በአጠቃላይ የትምህርት ጥራት መኖር ብቁና ተወዳዳሪ ምሩቃንን ለማፍራት የሚያስችል አመላካች ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም ነገ ሀኪም ሆነው ከበሽታችን የሚፈውሱን፣የህንጻ ጠበብት ሆነው ዘመን ተሻጋሪ ግንባታዎችን የሚሰሩልን፤ መምህር ሆነው ባለራዕይ ትውልድ ለመፍጠር የሚተጉ ዜጎችን ለማግኘት የዛሬው የትምህርት አሰጣጥ ጥራት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ማንም የማይክደው ሀቅ ነው፡፡
በደስታው ዋኘው
አርታኢ፡ ይዳኙ ማንደፍሮ
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

