ልዩ የእንቦጭ አረም ዘመቻ በጣና ሐይቅ
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ብናልፍ አንዱአለም፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዘዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ እና የሰ/ጎንደር ዞን የተለያዩ የመንግስትና የግል ቢሮ ሀላፊዎች፣ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ በማክሰኝት በኩል በሚገኘው በለምባ አርባይቱ ቀበሌ ተገኝተው ከቀበሌው ነዋሪዎች ጋር በጋራ በመሆን በጣና ሀይቅ ላይ በስፋት ተንሰራፍቶ የሚገኘውን የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ መስከረም 25/ 2009 ዓ.ም በተደረገው ልዩ ዘመቻ በቦታው በመገኘት አረሙን ሲያጸዱ ውለዋል፡፡
[widgetkit id=7091]
የእንቦጭ አረምን በሰው ኃይል የማስወገድ ዘመቻ ከተጀመረ ከ 1ወር በላይ ሁኖታል፡፡ በተለይም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለጣና ሐይቃችን ህልውና ስጋት የሆነውን ይህንን መጤ አረም ለማስወገድ በተደረጉት ዘመቻዎች ሁሉ ከፊት በመሰለፍ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ ለአብነትም ጥናትና ምርምሮችን ከመስራት በተጨማሪ የፋይናንስ እገዛ በማድረግ፣ በዘመቻው ወቅት የመጓጓዣ አቅርቦትን በማመቻቸት እና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ሀገራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ የሚታወስ ነው፡፡ በዚሁ ልዩ ዘመቻም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዘዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር፣ ባሉት የተፈጥሮና ባህላዊ ሀብቶች በዓለም የቅርስ መዝገብ በመስፈር ከኢትዮጵያ እና ከአፍሪካ አልፎ የዓለማችን ሀብት የሆነውን የጣና ሀይቃችንን ለመታደግ በተደረገው ዘመቻም ተገኝተው አረሙን በማስወገድ የዜግነት ሀላፊነታቸውን እንደተለመደው ሁሉ ሲወጡ ውለዋል፡፡
በፍጥነት በሀይቁ ላይ በመስፋፋት ላይ የሚገኘውን ይህንኑ መጤ አረም ለማስወገድ በተደረገው ልዩ ዘመቻ በወቅቱ ለተሳተፉት በጎንደር ዙሪያ ለሚገኙ የለምባ አርባይቱ ቀበሌ ነዋሪዎች የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት “ምንም እንኳ እናንተ በጣና ሀይቅ ዳርቻ አካባቢ የምትገኙ አርሶአደሮች አስከፊ አረሙን ለማስወገድ ከ 2004 ዓ.ም ጀምሮ ጥረት ብታደርጉም፣ አረሙ በሁሉም አካሉ ማለትም በግንዱ፣ በፍሬውና በቅጠሉ መራባት መቻሉ ከአቅም በላይ በመሆን እና ወሰኑን በማስፋት አሁን ካለበት አስከፊ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አስችሎታል፡፡ በመሆኑም የዚህ የእንቦጭ አረምን ጉዳይ ሀገራዊ ትኩረት እንዲሻ በማድረግ በማንኛውም መልኩ አረሙ ከጣና ሀይቅ ሙሉ በሙሉ ለማጽዳት በሚደረገው ርብርብ የክልሉ መንግስት ከጎናችሁ መቆሙን ለማብሰር ዛሬ ከናንተ ጋር አረሙን ለማስወገድ በተደረገው ልዩ ዘመቻ አብረናችሁ የማፅዳቱን ስራ በጋራ በመስራት ቆይታ አድርገናል፡፡ እንደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያሉ የክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች አረሙን ማጥፋት የሚያስችል የተለያዩ ምርምሮችን እያደረጉ ያሉበት ደረጃ ቢሆንም የምርምር ውጤቶቹ ውጤታማነታቸው ተረጋግጦ ተግባራዊ እስኪሆኑ ድረስ የሰው ሀይልን መጠቀም አይነተኛ አማራጭ በመሆኑ ወደ ኋላ ሳንል፣ ሳንሰለችና ጊዜ ሳንሰጥ ይህን ሀገራዊ ጠላታችንን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቆርጦ መነሳት አለበት፡፡ በርቱ እንበርታ፣ የእንቦጭ አረምን ከጣና ሀይቅ እናጥፋ” በማለት ነበር የተከበሩ ርዕሰ መስተዳደሩ ጠንከር ያለ መልክታቸውን ያስተላለፉት፡፡
ዩኒቨርሲቲያችንም ይህን አስከፊ አረም ሙሉ በሙሉ ለማፅዳት በሚደረገው ርብርብ (ጥናት እና ምርምሮችን በማድረግ፣ በፋይናንስ በማገዝ፣ የሰርቢስ አቅርቦትን በማመቻቸት እና ሌሎች አስፈላጊ እገዛዎችን በማድረግ) እንደተለመደው ሁሉ የፊታውራሪነቱን ድርሻ ለመውሰድ ተግቶ እየሰራ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በርቱ እንበርታ፣ ጣናችንን እንታደግ!
በአምሳሉ ግዛቸው/የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

