የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባለ ተሰጥኦ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የኪነጥበብ ዝግጅታቸውን አቀረቡ
ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ስኮላርስ ፕሮግራም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከዳግማሮስ ኢንተርቴይንመንትና ኢቬንትስ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የተሳተፉበት የኪነጥበብ ዝግጅት በማራኪ ግቢ ዛሬ 29 ቀን 2015 ዓ.ም ቀረበ፡፡
በእለቱ በርካታ እንግዶች የተገኙ ሲሆን ዶ/ር አስራት አፀደወይን ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት፤ ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚደንት፤ ዶ/ር ሞላልኝ በላይ፣ የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ስኮላርስ ፕሮግራም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዳይሬክተር፤ እንዲሁም የእለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት ኮሚሽነር ርግበ ገብረሀዋርያ፣ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ተማሪዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የዝግጅቱ ታዳሚ ለመሆን ችለዋል::
የማስተር ካርድ ፋንውዴሽን ስኮላርስ ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሞላልኝ በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው ስኮላርስ ፕሮግራሙ አካል ጉዳተኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ተማሪዎች የትምህርት እድል በመፍጠርና አቅማቸውን በመገንባት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የገለፁ ሲሆን በተጨማሪም ፕሮግራሙ ከኦኩፔሽናል ቴራፒ(Occupational Therapy) ፕሮግራም ጋር በተያያዘ አበረታች ስራ እየሰራ መሆኑንና በመጪው አመት በአካል ጉዳትና ማህበረሰብ አቀፍ ማቋቋሚያ ፕሮግራም(CBR) ዙሪያ በአለምአቀፍ ደረጃ ኮንፈረንስ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ዶ/ር አስራት ዓፀደወይን በዝግጅቱ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሰባት አስርት ዓመታት ጉዞው በሀገራችን እድገት ውስጥ በርካታ ውጤት ያስመዘገበ ሲሆን በተለይ ማህበረሰብ ተኮር የሆኑ ችግር ፈች ጥናትና ምርምሮችን በማካሔድ እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ በከፍተኛ የት/ት ተቋማት በኩል ግንባር ቀደም የሚያስብለው አመርቂ ውጤቶች እያስመዘገበ እንደሆነ የገለፁ ሲሆን በተለይ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ባሻገር በአካል ጉዳተኞችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በንቃት በመሳተፍና ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት ላይ ይገኛል ብለዋል። አክለውም ዩኒቨርሲቲው ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የማህበረሰብ አቀፍ ማቋቋሚያ ፕሮግራም በመሳሰሉ ሰፊና ዘላቂ ፕሮጀክቶች ውስጥ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችንና የማህበረሰብ ክፍሎችን በማካተት ተጠቃሚ ለማድረግ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫና አቅም መገንቢያ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡ በተያያዥም ዩኒቨርሲቲው የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ስኮላርስ ፕሮግራምን ተወዳድሮ በማሸነፍ ለ450 ባለ ራዕይ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት እንደተመቻቸ ገልፀዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አካታች የትምህርት ስነ-ዘዴን ተግባራዊ በማድረጉ በአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ተመራጭ ሊሆን እንደቻለ ገልጸዋል፡፡
በዛሬው እለት “እንችላለን!” በሚል ርዕስ የቀረበው የኪነጥበብ ዝግጅትም ከአካል ጉዳት ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የአመለካከት ችግር ለመቅረፍ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወትና ተሰጥኦ ያላቸው አካል ጉዳተኛ ታዳጊዎች ችሎታቸውን የሚያሳዩበት ተጨማሪ እድል እንደሚፈጥርም ገልፀዋል፡፡
ኮሚሽነር ርግበ በበኩላቸው ለታዳሚዎች አበረታች መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች አቅማቸውን እንዲጠቀሙ እድል በመፍጠርና የአካል ጉዳተኞች ሰብዓዊ መብት ዙሪያ አርአይ የሚሆን ስራ እየሰራ እንደሆነ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡