ለራስ አገዝ ቡድን ተወካዮችና ድጋፍ ለሚሰጡ ባለሙያዎች በስርዓተ ፆታ ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ጥር 2/2012 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ድጋፍ አብርጅሀ እና ጎርጎራ አካባቢ ለሚገኙ ለራስ አገዝ ቡድን ተወካዮችና ድጋፍ ለሚሰጡ ባለሙያዎች፣ ለታዋቂ ወንዶች እና ሌሎች ጥሪ ለተደረገላቸው አካላት በጎርጎራ መዝናኛ አዳራሽ በስርዓተ ፆታ እና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠና ሰጠ፡፡ በስልጠናው የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ባለሙያዎች እንዲሁም የወረዳ ሴቶችና ህፃናት ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

ፕሮግራሙን የዩኒቨርሲቲው የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ስመኝሽ ቸኮል በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት ሲሆን፣ ዳይሬክቶሬቱ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የማህበረሰቡን ችግሮች በጋራ ለመፍታት ይቻል ዘንድ በተለያዩ ወረዳዎች የገጠር ሴቶችን በራስ አገዝ ቡድን በማደራጀት ማብቃት በሚል ለሚዘጋጁ ስልጠናዎች በበጀት እየደገፉ እንደሚገኝ አውስተዋል፡፡ ወ/ሮ ስመኝሽ አያይዘውም ስልጠናው ሲዘጋጅ ሴቶች በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑና ተጠቃሚነታቸው የበለጠ እንዲረጋገጥ በጋራ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ስልጠናውን የኮሌጁ ም/ዲን ዶ/ር አስማማው አለሙ በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩ ሲሆን፣ በንግግራቸው ኮሌጁ በርካታ የማህበረሰብ አገልግሎቶች እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀው፣ ከነዚህም መካከል ባለፉት አመታት ውጤታማ የነበረው የገጠር ሴቶችን በራስ አገዝ ቡድን ማደራጀት አንዱ እንደሆነና ሴቶችን በማደራጀትና አራሳቸውን እንዲችሉ ማገዝ በሚል ተነሳሽነት ብዙ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በራስ አገዝ የተደራጁ ሴቶችን ወደ ህብረት የማደራጀት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ ይህንን ስልጠና እንዲሰጥ የበጀት ድጋፍ ያደረገውን የዩኒቨርሲቲውን ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬትን አመስግነዋል፡፡

በመቀጠል የገጠር ሴቶች የራስ አገዝ ቡድን ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ከፋለ እንዬው፣ በፕሮጀክቱ ከ2010ዓ/ም ጀምሮ እስከ አሁን የተሰሩ ስራዎችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ የልማትና የስርዓተ ፆታ ፅንሰ ሀሳብ በሚል አቶ ግርማው ፀጋዬ፣ ስርዓተ ፆታ ላይ መሰረት ያደረገው የስራ ክፍፍል እና ስርዓተ ፆታ፣ፆታ ላይ መሰረት ያደረገ ጥቃትን አስመልክቶ ወ/ሮ ትግስት ጴጥሮስ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአቶ አገሬ ነጋ፣ በስራ ፈጠራና ንግድ አስተዳደር ዙሪያ ፣ በአቶ ጥላሁን አዳሙ ደግሞ የተቀናጀ ተግባር ተኮር ትምህርት አሰጣጥ ለራስ አገዝ ቡድን አባላት በሚል ስልጠናው ተሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም የተሰጠውን ስልጠና እና አጠቃላይ ያለውን የስራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ጥያቄና አስተያየት ተሰጥቶ ሰፊ ውይይት ከተካሄደ በኋላ በኮሌጁ ም/ዲን በዶ/ር አስማማው አለሙ የመዝጊያ ንግግር ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡



