በህግ ዙሪያ የስራ ላይ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁራን በሰሜን ጎንደር ዞን በጃን አሞራና በየዳ ወረዳ ለሚገኙ የቀሌ ማህበራዊ ፍ/ቤት ዳኞችና አስተዳዳሪዎች የስራ ላይ አቅም ማጎልበቻ ስልጠና ከጥር 20 – 21/2012 ዓ.ም በድል ይብዛ ከተማ ሰጥተዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ት/ቤት ዲን አቶ አበበ አሰፋ፣ የበየዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደገኝ ውብነህ፣ ከ100 በላይ የሚሆኑ የየቀበሌው አስተዳዳሪዎችና የማህበረሰብ ፍ/ቤት ዳኞች በስልጠናው ተሳትፈዋል፡፡

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደገኝ የእንኳን መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሁለንተናዊ የሆነ የማህበረሰብ ለውጥ በአካባቢው እንዲመጣ እየተጋ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የማህበረሰብ ፍ/ቤት ዳኞች በዘልማድ የሚሰሩበትን የህግ አግባብ የዩኒቨርሲቲው የህግ ምሁራን በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ለማስቻል ብዙ ኪ/ሜትሮችን ተጉዘው ቦታው ድረስ በመምጣታቸው አቶ ታደገኝ ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የአካባቢው ማህበረሰብ ባህሉንና ወጉን ጠብቆ እንደሚገኝ ባደረገልን አስደሳች ኢቲዮጵያዊ አቀባበል አሳይቶናል ያሉት የስልጠናው አሰልጣኝ የነበሩትና ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው የህግ ት/ቤት ዲን አቶ አበበ ናቸው፡፡ የማህበረሰብ ፍ/ቤት ዳኞች በየቀበሌው ተ ቋቁመዋል፤ የማህበራዊ ፍ/ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ 246/2009 እና በፊት የነበረው አዋጅ 151/2000 እንደሚለው “ማንበብና መጻፍ” የሚችል ማንኛውም ግለሰብ የዚህ የማህበራዊ ፍ/ቤት ዳኛ መሆን ይችላል ይላል፡፡ ነገር ግን “የህግ እውቀት” ያለው ሰው አይልም፤ በመሆኑም ይህን ክፍተት ለመሙላት ይህ ስልጠና አስፈልጓል ብለዋል፡፡ አቶ አበበ::

የዩኒቨርሲቲው ህግ ት/ቤት ዲን አያይዘውም ህግ በቀጥታ ከሰው መብት ጋር ስለሚያያዝ የቀበሌ ፍ/ቤት ዳኞች በትንሹም ቢሆን ስለ ህግ መነሻ እውቀት ሊኖራቸው ይገባል ካልሆነ ግን ፍርድ በማዛባት ማህበረሰቡን ከመጉዳት ባሻገር እራሳቸው ዳኞቹ በሚሰጡት ኢ-ፍታዊ ፍርድ ተጠያቂ የሚሆኑበት አጋጣሚ ይፈጠራል ብለዋል፡፡ ስልጠናውን በመስጠት በኩል አንጋፋው የህግ መ/ርና ጠበቃ አቶ ተራመድ ተዛራ በንቃት ተሳትፈዋል፡፡
ያነጋገርናቸው ሰልጣኞች፣ ስልጠናው የነበረባቸውን የህግ ክፍተት በመሙላትም ሆነ ያላቸውን የህግ ኃላፊነትና ተጠያቂናት በግልጽ እንድንመለከት ረድቶናል ብለዋል፡፡



