የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአባይ ባንክ አክስዮን ማህበር ጋር የጋራ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና የአባይ ባንክ አክስዮን ማህበር ለሰራተኞች የብድር አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የጋራ የመግባቢያ ሰነድ የካቲት 02/2012 ዓ/ም በሳይንስ አምባ አዳራሽ ተፈራርመዋል፡፡

ፕሮግራሙን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን በንግግር ከፍተዋል፡፡ በንግግራቸውም በበጀት ዓመቱ ሊሰሩ ከታቀዱ ስራዎች አንዱ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ የብድር ተጠቃሚ ማድረግ መሆኑን ገልፀው፣ የሚገኘው ብድርም ለቤት መስሪያ ወይም መግዣ፣ ለመኪና መግዣ እና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ዶ/ር አስራት ዩኒቨርሲቲው ሰራተኛውን የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ ወለዱ አነስተኛ የሆነ እና አገልግሎት አሰጣጡ የተሻለ የሆነውን የአባይ ባንክ አክሲዮን ማህበርን እንደመረጡ የገለፁ ሲሆን፣ ለዚህም የዩኒቨርሲቲውን ከፍተኛ አመራሮች፣ የሚመለከታቸው ዳይሬክተሮችና የአባይ ባንክን የጎንደር አካባቢ ስራ አስኪያጅን ከዚህ ደረጃ እንዲደርስ ላደረጉት ርብርብ አመስግነዋል፡፡

የጎንደር አካባቢ የአባይ ባንክ አክሲዮን ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሽባባው ሙጬ ደግሞ ሰራተኞች ብደር ለመውሰድ ሊያሟሏቸው የሚገቡ ነጥቦችን በዝርዝር ካቀረቡ በኋላ በተሰብሳቢዎች በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች በተገኙበት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በኩል የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን እና በአባይ ባንክ አክሲዮን ማህበር ደግሞ የጎንደር አካባቢ የአባይ ባንክ ስራ አስኪያጅ በአቶ ሽባባው ሙጬ በኩል የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡



