የመማር ማስተማር አቅምን ማጎልበት የሚያስችል ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስነ ትምህርት ኮሌጅ በተማሪ ተኮር ማስተማር ስነ ዘዴ፣ በተግባር ተኮር ምርምር እና በትምህርት ቤት ማሻሻል ዕቅድ ዙሪያ ከሰሜን ጎንደር ዞን ለተውጣጡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች የትምህርት ባለሙያዎች እንዲሁም ርዕሳነ መምህራን ስልጠና ሰጠ፡፡ ስልጠናውን የኮሌጁ የትምህርት እቅድ እና ስራ አመራር ትምህርት ክፍል መምህራን፣ አቶ ጌትነት አለነ፣ አቶ ጀምበሩ አረጋ እና አቶ አበበ ምንአልኩለት በጋራ ሰጥተዋል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ተማሪ ተኮር የማስተማር ስነ ዘዴ ተግባራዊ ስለማይደረግ በተለይም አብዛኛው መምህራን የሚጠቀሙት መምህር ተኮር የማስተማር ስነ ዘዴን በመሆኑ፣ መምህራን እና የትምህርት ባለሙያዎች በእነዚህ ጉዳዮች ያላቸውን አቅም ማጎልበት እንዲሁም መምህራንን ለማነቃቃት ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱን በኮሌጁ መምህር የሆኑት አቶ ጌትነት አለነ ገልፀዋል፡፡

ይህም የትምህርት ውጤትን የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርግ እና የመማር ማስተማር አቅምን ማጎልበት እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡

የተሰጠው ስልጠና ውጤታማ እንዲሆን ከወራት በኋላ ያለውን ለውጥ በመከታተል የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ዝግጁ መሆናቸውን እና እቅድ መያዙንም አሰልጣኞች ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ስልጠና በማክሰኝት ከተማ መሰጠቱን እና ወደፊትም ስልጠናው በቆላድባ ከተማ እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡



