የጤና ተቋማት ተገልጋዮችና ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19)
ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በሽታዉን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመግታትና ለመቆጣጠር በሀገር አቀፍ ደረጃ ክትትል የሚሹ የተለያዩ ወሳኝ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ ናቸው::
ከዚህ ጋር በተያያዘ በዚህ ወቅት ወደ ሆስፒታል ወይም ወደ ማንኛውም ጤና ተቋም የሚመጡ የታካሚዎችን፣ የአስታማሚዎችንና የጠያቂዎችን ቁጥር ለተገልጋዮች፣ ለቤተሰባቸውና ለማህበረሰብ ደህንነት ሲባል መቀነስ የግድ ይላል::
ስለሆነም ታካሚዎች፣ አስታማሚዎችና ጠያቂዎች የሚከተሉትን ምክረ ሃሳቦች መተግበር ቢችሉ የበሽታዉን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበርክታሉ::
ሀ. ታካሚዎች
ድንገተኛ እና አጣዳፊ ህመም ካልተከሰተ ወይም ክትትል የሚሻ የጤና ችግር ከሌለ በስተቀር ወደ ጤና ተቋም አለመሄድ:: ከዚህ በተጨማሪም ለኮሮና በሽታ ከፍተኛ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ማለትም እድሜአቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ፣ የልብ ችግር ያለባቸው፣ የመተንፈሻ አካል ህመም (ለምሳሌ አስም) ያለባቸው፣ የስኳር ህሙማን፣ የካንሰር ታማሚዎች፣ ወዘተ የሚወስዱትን መድሃኒት/ቶች በአግባቡ እየወሰዱ በተቻለ መጠን ከቤት አለመዉጣትና ከሰዎች ጋር ንክኪን በማስወገድ እራስን ከኮሮና ቫይረስ መጠበቅ:: በራስ ለመወሰን አስቸጋሪ ሁኔታ ከገጠመ በ8335 ወይም በ444 ወይም ሌሎች ክልላዊ መስመሮች/የተቋማት ስልክ ቁጥሮች ደዉሎ ምክረ ሃሳብ መጠየቅ::
ለ. አስታማሚዎች
ለህክምና ወደ ሆስፒታል የሚሄዱ ታካሚዎች (ከህፃናት/ልጆች/አቅመ ደካሞች በስተቀር) ከተቻለ ያላስታማሚ መሄድ:: አስታማሚ ይዞ መሄድ የግድ ከሆነ ደግሞ አስገዳጅ ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ አንድ አስታማሚ ብቻ አብሮ እንዲሄድ ማድረግ::
ሐ. ህሙማን ጠያቂዎች
ወደ ሆስፒታልና ጤና ተቋማት ከመሄድ ተቆጥቦ በስልክ ብቻ ከታካሚዎች/ከአስታማሚዎች/ከቤተሰብ ጋር ግንኙነት ማድረግ::
እነዚህ ተግባራት የኮሮና በሽታ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ እገዛ ከማድረጋቸዉም ባሻገር በጤና ተቋማትና ሙያተኞች ላይ የሚደርሰውን መጠነ ሰፊ ጫና ለመቀነስ ወሳኝ ናቸው:: በተጨማሪም የጤና ተቋማት ያላቸውን ዉስን የሕክምና ግባት እንዲቆጥቡና ቅድሚያ ለሚሰጠው ታካሚ ቅድሚያ ሰጠው ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል::
ይህ ወረርሽኝ የጤና ስርዓቱን ከማዳከሙ ባሻገር የሀገር ኢኮኖሚን ስለሚያደቅ ያለውን ዉስን ሃብት በአግባቡ መጠቀም እንዲቻል ተገልጋዮች ግለሰባዊና ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት የጤና ተቋማት መደበኛ ስራቸውን መቀጠል እንዲችሉ ማገዝ ይኖርባቸዋል::
እግዚአብሔር በምህረቱ ይጎብኘን!
ዶ/ር ወርቅአገኘሁ ኃይሉ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር እና የኩላሊትና የውስጥ ደዌ ህክምና ስፔሻሊስት።



