የ2012 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎች እና የ5ኛ አመት የህክምና ተማሪዎች የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ትንንሽ ፕሮጀክቶችን (mini projects) አስመረቁ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ2012 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎች እና የ5ኛ አመት የህክምና ተማሪዎች በመስክ ላይ የቡድን ስልጠና (TTP) ፕሮግራም የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ትንንሽ ፕሮጀክቶችን (mini projects) በመስራት መጋቢት 11/2012 ዓ.ም አስመርቀዋል፡፡ እነዚህን ፕሮጀክቶች ያስመረቁት በቆላድባ፣ በጠዳ፣ በማክሰኝት፣ በአዲስዘመን እና በወረታ በነበራቸው የመስክ ላይ የቡድን ስልጠና ቆይታቸው ነው፡፡

ተማሪዎቹ የቲቲፒ ቢሮ በሚያዘጋጃቸዉ የዳሰሳ ጥናት መጠይቆች መሰረት በየተመደቡበት አካባቢ የሚኖረውን የማህበረሰብ ችግር ለመፍታት በማረሚያ ቤቶች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ጣቢያዎች፣ በሀይማኖት ተቋማት እንዲሁም ሰዎች በጋራ በሚኖሩባቸው አንዳንድ አካባቢዎች በመገኘት ዳሰሳዊ ጥናቱን አካሂደው ችግሮቹን ይለያሉ፡፡ ችግሮቹ ከተለዩ በኋላ ደግሞ እነኝህን የማህበረሰብ የጤና ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ፕሮጀክቶች በመንደፍና ልዩ ልዩ አጋር አካላትን በማፈላለግ ፕሮጀክቶችን በመስራት የማህበረሰቡን ችግር ሲፈቱ ቆይተዋል፡፡

በዚህ ዙር የቲቲፒ ፕሮግራም ፕሮጀክቶች መካከልም በቆላድባ ከተማ ባለ ስድስት ክፍል የህዝብ መፀዳጃ ቤት እና ለታራሚዎች አገልግሎት የሚውል ሴፍቲ ታንከር የገነቡ ሲሆን በተመሳሳይ በሌሎች ወረዳ እና የከተማ ሳይቶችም የመፀዳጃ ቤቶች፣ ለታካሚዎች የልብስ ማጠቢያ ገንዳ፣ ለሴት ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያ (ሞዴስ) መቀየሪያ ክፍል ገንብተዋል፡፡

ተማሪዎቹ በመስክ ላይ የቡድን ስልጠና ቆይታቸው በርካታ ልምድና ተሞክሮ ማግኘታቸውን፣ በተለይ የማህበራዊ ህይዎት ግንኙነታቸው ምን መምሰል እንዳለበት እና ችግሮች ሲያጋጥሙ እንዴት መፍታት እንደሚቻል መማራቸውን የፕሮጀክት ስራዎቻቸውን ሲያሰመርቁ ባዘጋጁት መርሀ ግብር ተናግረዋል፡፡
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



